ቀጥታ፡

የዒድ አል-ፈጥር በዓልን በአብሮነትና በመረዳዳት ማሳለፍ ይገባል

ዲላ፤ መጋቢት 10/2018(ኢዜአ)፦ የዒድ አል-ፈጥር በዓልን በኃይማኖቱ አስተምህሮቱ መሠረት በአብሮነትና በመረዳዳት ማሳለፍ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የእስልምና እምነት አባቶች ገለፁ።

የኢድ-አልፈጥር በዓል ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር አብሮነትና ማህበራዊ ትስስርን ያጠናክራል

በፆም ወቅት የታየው የመረዳዳት እና የመደጋገፍ እሴት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተመላክቷል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኡላማዎች ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢና የዲላ ከተማ ቢላል መስጅድ ዋና ኢማም ሼህ ሰኢድ መሐመድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የረመዳን ወር በጾምና በፀሎት ከማሳለፍ ባለፈ የመረዳዳት ባህል የታየበት ነው።  


 

ኢድ የመደሰት፣ የመረዳዳትና የመደጋገፍ በዓል ነው ያሉት ሰብሳቢው ኃይማኖታዊ ትዕዛዝን መሠረት ባደረገ መልኩ ለማክበር ተዘጋጅተናል ነው ያሉት።

በተለይም ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወር ያሳየውን ፍቅር እና አንድነት በማስቀጠል ለሀገር እድገት መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

በዓሉን ከስግደት እና ከፀሎት ባሻገር እርስ በእርስ በመረዳዳት፣ የፈጣሪን ትዕዛዝ በማክበር ለማሳለፍ ተዘጋጅተናል ያሉት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ኢንጂነር ጠሀ ረዲ ናቸው።


 

በረመዳን ወቅት ያለው ለተቸገሩ ወገኖች በማካፈል ኃይማኖታዊ ትዕዛዝ መሆኑን ያነሱት ዋና ጸሐፊው ይህንኑ ቅዱስ ተግባር በበዓሉ ወቅት በማከናወን ግዴታችንን መወጣት አለብን ብለዋል።

የዲላ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ኡስታዝ አብድራህማን አብድቁ በበኩላቸው፤ የረመዳን ወር የአምልኮ ስርዓትን በማጠናከር እና በመደጋገፍ ማለፉን ጠቅሰዋል።


 

በዚህን ወቅት ፈጣሪን ከማመስገን ባለፈ እያንዳንዱ የእምነቱ ተከታይ ካለው ላይ ለሌላቸው በማካፈል በዓሉን እንዲያሳልፍ አመልክተዋል።

በመሆኑም በዓሉን በመረዳዳት እና በመደጋገፍ በጋራ ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም