የኢድ-አልፈጥር በዓል ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር አብሮነትና ማህበራዊ ትስስርን ያጠናክራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢድ-አልፈጥር በዓል ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር አብሮነትና ማህበራዊ ትስስርን ያጠናክራል
ወልቂጤ፤ መጋቢት 10/2018 (ኢዜአ)፦የኢድ-አልፈጥር በዓል ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር የመረዳዳት፣ አብሮነትና ማህበራዊና ሕዝባዊ ትስስርን የሚያጠናክር መሆኑ ተመላከተ።
በወልቂጤ ከተማ የክርስትና እና እስልምና እምነት ተከታዮች በጋራ በመሆን የኢድ-አልፈጥር በዓል ማክበሪያ ስፍራን አፅድተዋል።
በጽዳት መርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉ የክርስትና እምነት ተከታዮችም ከእስልምና እምነት ተከታይ ወገኖቻቸው ጋር ያላቸውን አብሮነት ለማሳየት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢድ ዝግጅት ኮሚቴ አስተባባሪ ወጣት አቡበከር አምሩ፤ በነገው እለት የሚከበረውን የኢድ አልፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ የክርስትና እምነት ተከታዮች የመስገጃ ስፍራውን አብረውን በማጽዳታቸው ተደስተናል ብሏል።
የኢድ በዓል ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር የመረዳዳት፣ አብሮነትና ማህበራዊና ሕዝባዊ ትስስርን የሚያጠናክር ስለመሆኑ አንስቶ አብሮነታችን ይቀጥላል ሲል ተናግሯል።
በፅዳት መርሃ ግብሩ ላይ ከተሳተፉት መካከል ወጣት ታምራት መንግስቱ፤ ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት ልዩነት ቢኖረንም በማህበራዊ ትስስር ረገድ ጥብቅ ቁርኝት አለን ብሏል።
በመሆኑም በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በነገው እለት የሚከበረውን የኢድ አል-ፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ የመስገጃ ስፍራቸውን በጋራ አጽድተናል ሲል ተናግሯል።
ደም በመለገስ፣ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና ማዕድ በማጋራት እንዲሁም የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ላይ እየተሳተፈ መሆኑንም አንስቷል።
ሌላኛዋ የመርሃ ግብሩ ተሳታፊ ወጣት ቤተልሄም አያሌው የፅዳት መርሃ ግብሩን ያከናወኑት ለማህበረሰቡ አብሮነታችንን ለማሳየት ነው ብላለች።
አማኞች ውብ በሆነ አካባቢ ኢድ-አልፈጥርን በድምቀት እንዲያከብሩ በማሰብ በፅዳቱ መርሃ ግብር ላይ ለመሳተፍ እንደተነሳሳች ገልፃለች።
የኩኑዝ በጎ አድራጎት ማህበር ሰብሳቢ ወጣት አሚር አወል ከክርስትና እምነት ተከታይ ወጣቶች ጋር በመሆን የኢድ ሶላት መስገጃ ቦታን በማጽዳት ጠንካራ ትብብርና አብሮነታችንን አሳይተናል ብሏል።
በረመዳን ወር የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር 700 ለሚጠጉ ወገኖች የዘይት፣ የሩዝ እና የዱቄት ድጋፍ ማድረጋቸውን አንስቷል ።
የጉራጌ ዞን እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሰብሳቢ ኡስታዝ ዐባስ ያሲን ወጣቶቹ ባደረጉት መልካም አርዓያነት ያለው ተግባር መደሰታቸውን ገልጸዋል።
የወልቂጤ እና አካባቢው ህዝብ የእምነት ልዩነት ቢኖርም ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር ያለው በመሆኑ በዓላት ሲመጡ በመተሳሰብና አብሮነት የሚያከብሩ መሆኑንም ገልጸዋል።