የበጋ መስኖ ልማት አርሶ አደሮችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የበጋ መስኖ ልማት አርሶ አደሮችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እያደረገ ነው
ባህር ዳር ፤ መጋቢት 10/2018(ኢዜአ)፦የደቡብ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮች በበጋ መስኖ ልማት በምግብ ራሳቸውን ከመቻል ባለፈ ለገበያ በማቅረብ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው።
በምስራቅ ጎጃም ዞን ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ ነው
በአማራ ክልል በበጋ ወቅት በመስኖ ከለማ 500 ሺህ ሄክታር መሬት ከ51 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል።
በደቡብ ጎንደር ዞን የፎገራ ወረዳ አርሶ አደር ተዋቸው ፈጠነ ለኢዜአ እንደገለጹት የመስኖ ውሃ በመጠቀም ሁለት ሄክታር የሚጠጋ መሬታቸውን በሽንኩርት፣ ቃሪያና ጤፍ አልምተዋል።
በግማሽ ሄክታር ካለሙት ቀይ ሽንኩርት ቀድሞ የደረሰውን ከ90 ኩንታል በላይ ምርት በመሰብሰብ ለገበያ አቅርበው ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም ቀሪውን ቀይ ሽንኩርት፣ ቃሪያና የጤፍ ምርት ለገበያ በማቅረብ ካፒታላቸውን ለማሳደግ ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሌላው የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር ቸሬ መንግስት በበኩላቸው የመስኖ ልማት ሥራው በምግብ ራሳችንን እንድንችል ከማድረግ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነታችንን እያሳደገው ነው ብለዋል።
ሁለት ሄክታር መሬት ላይ በመስኖ ስንዴ፣ አጃ፣ ቀይ ሽንኩርትና ጤፍ ማልማታቸውን ጠቅሰው፣ ምርቱን ከቤት ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን በዘላቂነት ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የደረሰውን የቲማቲምና የሽንኩርት ምርት በመሰብሰብ ላይ እንደሆኑ የገለጹት ደግሞ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የጓንጓ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር የቆዬ ተመስገን ናቸው።
በመስኖ ልማት መሳተፍ ከጀመሩ ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ ገቢያቸው መጨመሩንና ኑሯቸው እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸው፣ ዘንድሮም ልማቱን አጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የመስኖ አግሮኖሚ ባለሙያ አቶ ንጋቴ አለማየሁ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በክልሉ ዘንድሮ 500 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ ወደስራ ተገብቷል።
እስካሁንም ከ481 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት የተቻለ ሲሆን፣ በልማቱ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በሁለት ዙር በመስኖ ከሚለማው መሬትም በአጠቃላይ ከ51 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
እንደ ባለሙያው ገለጻ በመጀመሪያ ዙር መስኖ ከለማው መሬት እስካሁን ድረስ ከ6 ሚሊዮን 881 ሺሀ ኩንታል በላይ የተለያዩ አትክልቶችና የሰብል ምርቶች ተሰብስበው ለገበያ ቀርበዋል።
በክልሉ ባለፈው ዓመት የበጋ ወራት ከለማው ከ331 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት 46 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።