በምስራቅ ጎጃም ዞን ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ጎጃም ዞን ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ ነው
ደብረ ማርቆስ፤ መጋቢት 9/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ለ2018/2019 የምርት ዘመን የሚውል ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ ዘመናዊ ማዳበሪያ ወደ ዞኑ ገብቶ ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው የግብዓት አቅርቦት ቡድን መሪ አቶ ኃይለኢየሱስ ዳምጤ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዞኑ ትርፍ አምራች በመሆኑ ምርታማነትን ለማሳደግ የግብዓት አቅርቦቱ ቀድሞ እንዲከናወን እየተደረገ ነው።
በዚህም ለመጪው የምርት ዘመን በአጠቃላይ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ ሥራዎች ተጀምረዋል።
እስካሁን በተደረገው ጥረትም ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ወደ ዞኑ የገባ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው በመሠረታዊ ማኅበራት በኩል ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ገልጸዋል።
ይህም በምርት ዘመኑ በእቅድ የተያዘውን 25 ሚሊዮን ኩንታል የምርት ግብ ለማሳካት ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው አስረድተዋል።