ቀጥታ፡

በጋሞ ዞን በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ በፍጥነት እንዲደርስ የተጀመረው የመንገድ ከፈታ ሥራው በቀጣይ ሶስት ቀናት ይጠናቀቃል

አርባ ምንጭ፤ መጋቢት 10/2018(ኢዜአ)፦ በጋሞ ዞን በተፈጥሮ አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ በፍጥነት እንዲደርስ የተጀመረው የመንገድ ከፈታ ሥራ በመጪዎቹ ሶስት ቀናት እንደሚጠናቀቅ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ።

በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ ቀጥሏል

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር እድሬ እርኮ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ አደጋው ከተከሰተባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ የማዞ ዶይሳ ቀበሌ ተሽከርካሪ መድረስ ከሚችልበት ቦታ በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።


 

በዚህም ምክንያት ለተጎጂዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ፈጥኖ እንዲደርስ ባለሥልጣኑ የጀመረው የመንገድ ከፈታ ሥራ እየተፋጠነ ይገኛል ብለዋል።

ከአደጋው አሳሳቢነት አንፃር ችግሩን በፍጥነት ለመፍታት በክልሉ የሚገኙ አብዛኞቹ ማሽነሪዎች ወደ አካባቢው እንዲሰማሩ የተደረገ ሲሆን፤ እስካሁንም 13 ኪሎ ሜትር መንገድ ለተሽከርካሪ ክፍት መደረጉን አስታውቀዋል።


 

ለተፈናቃዮች አስቸኳይ ምላሽ መስጠት እንዲቻል በቀጣይ ሦስት ቀናት ቀሪ የ7 ኪሎ ሜትር ሥራው እንደሚጠናቀቅም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም