በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ ቀጥሏል
አርባ ምንጭ ፤መጋቢት 9/2018 (ኢዜአ)፦በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ ቀጥሏል፡፡
በዛሬው ዕለትም የተለያዩ ተቋማት 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚገመት የምግብ፣ የአልባሳትና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።
የተለያዩ ተቋማት በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ
ኦርቢስ ኢንተርናሽናል፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የወጣቶች አደረጃጀቶች እንዲሁም ዳሽን ቢራ ፋብሪካ ለተጎጂዎች ያመጡትን ድጋፍ ዛሬ ለጋሞ ዞን አስተዳደር አስረክበዋል።
ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
የኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ፕሮግራም ማናጀር አቶ ሙላቱ ገብሬ፤ ከተቋሙና ከሠራተኞች በተሰበሰበ ገንዘብ የንፁህ ውሃና የንፅህና መጠበቂያዎችን ማስረከባቸውን ገልጸዋል።
በደቡብ ክልል ወጣቶች አደረጃጀት የወላይታ ዞን፣ የሶዶ ከተማና የአሪ ዞን መዋቅር አባላትና በጎ ፈቃደኞችም አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶች ክንፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚካኤል ዋዳ እንደገለፁት፤ አደጋው ከተከሰተበት እለት ጀምሮ የተለያዩ አደረጃጀት አባላት በነፍስ አድንና ሌሎች ተግባራት ሲሳተፉ ቆይተዋል።
የዛሬ የተደረገው የምግብና የዓይነት ድጋፍ በክልሉ ሁሉም መዋቅሮች ባሉ የወጣት አደረጃጀቶች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ ዳሽን ቢራ ፋብሪካ ለተጎጂዎች አፋጣኝ ምላሽ የሚውል ግምታቸው 1 ሚሊዮን ብር የሆነ የአልባሳት ድጋፍ አድርጓል።
የፋብሪካው ኮርፖሬት ጉዳዮች ኮሙኒኬሽን ማናጀር አቶ አብርሀም ዘሪሁን፤ በወገኖች ላይ በደረሰ አደጋ የፋብሪካው ሠራተኞችና አመራሮች በእጅጉ ማዘናቸውን ገልጸዋል።
ለተጎጂዎች አፋጣኝ ድጋፍ የሚሆንና ግምታቸው ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ብርድልብሶችን ዛሬ ማበርከታቸውን ገልፀው ድጋፉ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የጋሞ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ፤ የተጎዱ ወገኖች ከደረሰባቸው ችግር ፈጥነው እንዲያገገሙ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ምላሽ እየሰጡ ያሉ አካላትን አመስግነዋል።
በቀጣይ ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረው ጥረት ሁሉም ከጎናቸው በመሆን እንዲረባረብም ጥሪ አቅርበዋል።