የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በዜጎች አኗኗር እና ጤና ላይ መሰረታዊ ለውጥ እያመጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በዜጎች አኗኗር እና ጤና ላይ መሰረታዊ ለውጥ እያመጣ ነው
ወልቂጤ፤መጋቢት 10/2018 (ኢዜአ)፦ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በዜጎች አኗኗር እና ጤና ላይ መሰረታዊ ለውጥ እያመጣ መሆኑን የጤና ዘርፍ የስራ ሃላፊዎች ገለጹ።
አዋጁ እንደ ሀገር የተጀመረውን የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ከግብ ለማድረስ ያግዛል
የ"ፅዱ ኢትዮጵያ" ንቅናቄ በሀገሪቱ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን ለማሻሻል፣ የከተሞችን ውበት ለመጠበቅ እና ለዜጎች ምቹ የመኖሪያ አካባቢን ለመፍጠር ያለመ ሀገራዊ ዘመቻ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነት የተጀመረው ኢንሼቲቭ በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች ተግባራዊ እየተየደረገ ያለ መሆኑ ይታወቃል።
የ"ፅዱ ኢትዮጵያ" ዋነኛ ዓላማም በተለይም በከተሞች የሚታየውን የንፅህና ጉድለት በማስተካከል ለነዋሪዎችና ለጎብኝዎች ዘመናዊና ምቹ ከተሞችን የመፍጠር ነው።
በዚህም መሰረት የተገነቡ መሠረተ ልማቶችን በአግባቡ መጠገንና መጠበቅ፣ የቆሻሻ አወጋገድን የማዘመን፤ የመፀዳጃ ቤቶችን የማስፋትና የማዘመን ስራ በስፋትና በጥራት ማከናወን ተችሏል።
ከዚህ አንፃር በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በፅዱ ኢትዮጵያ ኢንሼቲቭ የተገኘውን ውጤት በተመለከተ የኢዜአ ሪፖርተር የጤና ዘርፍ ሃላፊዎችንና ነዋሪዎችን አነጋግሯል።
የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ አየለ ፈቀደ፤ በኢንሼቲቩ በገጠርም ይሁን በከተሞች ሰፊ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው ለስኬቱ በየደረጃው ያሉ የስራ ሃላፊዎችና አጠቃላይ የማህበረሰቡ ተሳትፎ የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።
ፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ብዙ ተያያዥ የሆኑ ማህበራዊና የምጣኔ ሃብት ጥቅሞች እያስገኘ መሆኑን የገለጹት ሃላፊው በቀጣይም በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል ብለዋል።
የአካባቢ ጽዳትና ውበትን በጋራ በመጠበቅና በመንከባከብ ምቹና ተመራጭ አካባቢ ለመፍጠር ዜጎችን በማሳተፍ ስኬት እየተመዘገበ ነው ብለዋል።
በሁሉም የዞኑ አካባቢዎች ፅዱ እና ለመኖርያነት ምቹ የሆኑ መንደሮች እንዲሁም ሜዳ ላይ ከመፀዳዳት ነፃ የሆነ አካባቢ ለመፍጠር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
እስካሁን በዞኑ ከሚገኙ 315 ቀበሌዎች መካከል 70 በመቶ ያህሉ የዚህ ኢንሼቲቭ ትግበራ ተጠቃሚዎች መሆን መቻላቸውንም ለአብነት አንስተዋል።
የሃድያ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ ዶ/ር ደሳለኝ ሽጉጤ፤ የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በየአካባቢው ካለው ማህበረሰብ ባለፈ ከጤና፣ ከትምህርት እና ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በቅንጅት መሰራቱ ውጤት አምጥቷል ብለዋል።
የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በዞኑ ህዝብ ጤና እና አኗኗር ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ በመሆኑ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
የምስራቅ ጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ ሰለሞን ጉግሳ፤ የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በዞኑ በርካታ ቀበሌዎች እና ወረዳዎችን ጽዱ አካባቢ ማድረግ አስችሏል ብለዋል።
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ ሳሙኤል ዳርጌ፤ የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በክልሉ መሰረታዊ የሚባል ውጤት የመጣበት ስኬታማ ትግበራ መሆኑን ገልጸዋል።
መርሃ ግብሩ የተሻሻሉ መፀዳጃ ቤት በመገንባት የሰውና እንስሳ መኖርያ በመለየት ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እያስቻለ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በክልሉ ዜጎች አኗኗር እና ጤና ላይ መሰረታዊ ለውጥ እያመጣ መሆኑን አንስተው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።
በጉራጌ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ነዋሪዎችም የፅዱ አካባቢ ልማት በቆሻሻ አወጋገድና አጠቃቀም ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል።