ቀጥታ፡

አዋጁ እንደ ሀገር የተጀመረውን የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ከግብ ለማድረስ ያግዛል

አሶሳ፤ መጋቢት 4/2018(ኢዜአ)፦የተሻሻለው የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ አዋጅ እንደ ሀገር የተጀመረውን የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ከግብ ለማድረስ እንደሚያግዝ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አካባቢና ደን ጥበቃ እና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን አስታወቀ።

በክልሉ ህብረተሰቡ በፕላስቲክ ከረጢት ምትክ አማራጭ ምርቶችን በስፋት እንዲጠቀም እየተደረገ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ፣ የወንዝ ዳርቻ፣ የከተማና ገጠር ኮሪደር ልማት ስኬቶች ጤናማ የአካባቢ ሥነ-ምኅዳር መፍጠር አስችለዋል

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሉቅማን አብዱልቃድር እንዳስታወቁት፤ የተሻሻለውን የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ አዋጅ በክልሉ ተግባራዊ ለማድረግ በተለያዩ መድረኮች ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ተደርጓል።

በዚህም በፕላስቲክ ምርት ንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች አማራጭ ምርቶችን ማምረት እንዲጀምሩ በተግባር የታገዘ የሙያ ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በአሁኑ ሰዓት የተወሰኑ ግለሰቦች ተኪ ምርቶችን ማዘጋጀት መጀመራቸውን ጠቁመው፥ በዘርፉ ላይ ለሚሰማሩ አካላት አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።


 

የፕላስቲክ ከረጢቶች ለአካባቢ ብክለት መንስኤ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ሉቅማን አዋጁ እንደ ሀገር የተጀመረውን የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ከግብ ለማድረስ ያግዛል ብለዋል።

አዋጁን ተከትሎ የፕላስቲክ ከረጢቶችን የሚተኩ ምርቶች ላይ የተሰማራችው ወጣት ጅራቱ ሰንበቶ በበኩሏ፤ አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ይገባል ብላለች።

በቅርቡ ወደ ስራ መግባቷን ገልጻ አዲስ አበባ በመሄድ ሙያዊ ስልጠና መውሰዷን ተናግራለች።


 

በአሁኑ ሰዓት ሌሎች በዘርፉ የሚሰማሩ የስራ ዕድል ተጠቃሚዎችን ለማሰልጠን ፍላጎት እንዳላት ገልጻ ጎን ለጎንም ለንግድ ተቋማት  የወረቀት ከረጢቶችን በማዘጋጀት የማስተዋወቅ ስራ እያከናወነች መሆኑን ተናግራለች።

አዋጁን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ በማድረግ የፕላስቲክ ከረጢቶች የሚያደርሱትን የአካባቢ ብክለትና በህብረተሰቡ ላይ የሚያስከትሉትን የጤና ጠንቅ መከላከል እንደሚገባም ነው የገለጸችው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም