ቀጥታ፡

ካርድ በመውሰድ ለሀገር ይበጃል የምንለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል-የሮቤ ከተማ ነዋሪዎች

ሮቤ ፤መጋቢት 10/2018 (ኢዜአ)፦ በጠቅላላ ምርጫው ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ በመውሰድ ለሀገር ይበጃል ያሉትን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን የሮቤ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ለመምረጥ የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ እየወሰዱ ይገኛሉ

በብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል። 

በባሌ ዞን ሮቤ ከተማ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመራጭነት የሚያበቃቸውንና ለሀገር ይበጃል ብለው ለሚያምኑት የፖለቲካ ፓርቲ ድምጻቸውን ለመስጠት የሚያስችላቸውን ካርድ አስቀድመው መውሰዳቸውን አመልክተዋል።

በከተማዋ የጄኔራል ዋቆ ጉቱ አደባባይ አካባቢ በጫማ ማስዋብ ሥራ የሚተዳደረው አካል ጉዳተኛ ዘውዱ ከበደ፤ የመራጭነት ካርድ ከወሰዱ ነዋሪዎች መካከል ነው።


 

"የምርጫ ካርዴ ነገ ለሀገር የተሻለ ሥራ የሚሠራ ፓርቲን የምመርጥበት ነው" ያለው ዘውዱ፣ መብቱን ለመጠቀም መመዝገቡንና ሌሎች ወጣቶችም ፈለጉን እንዲከተሉ ጥሪ አቅርቧል። 

ወንድማማቾቹ ወጣት መሐመድ ኢድሪስ እና ሐሰን ኢድሪስ በጋራ በመሆን በአቅራቢያቸው በሚገኝ የዜበላ ወለሼ የምርጫ ጣቢያ በመገኘት የመራጭነት ካርድ ወስደዋል። 

ወጣት መሐመድ በሰጠው አስተያየት፣ "ምርጫ የዜግነት መብታችንን የምንጠቀምበትና የሀገራችንን የወደፊት እጣ ፈንታ የምንወስንበት መድረክ በመሆኑ ቀድመን ካርድ መውሰድን መርጠናል" ብሏል። 


 

የምዝገባ ሂደቱም ቀላልና ቀልጣፋ በመሆኑ ሌሎችም መራጮች የመመዝገቢያው ጊዜ ሳያበቃ ካርድ ሊወስዱ እንደሚገባ አሳስቧል።

ወጣት ሐሰን ኢድሪስ በበኩሉ፣ የምርጫ ካርድ መያዝ የዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ መጀመሪያ መሆኑን ጠቅሶ፣ "እኛ ወንድማማቾች እንደመሆናችን በጋራ መጥተን ተመዝግበናል፤ ሌሎችም ቤተሰቦችና ጎረቤቶች ተቀናጅተው በመምጣት ካርዳቸውን ሊወስዱ ይገባል" ሲል ነው መልዕክት ያስተላለፈው።


 

በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ ነፍሰ ጡር እናቶችና አካል ጉዳተኞች ለምዝገባ ሲመጡ ቅድሚያ እንዲያገኙ መደረጉ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ የስርባ መሐመድ ናቸው። 

በተለይም ሴቶች በቤተሰብና በማኅበራዊ ሕይወት ያላቸውን ሚና ወደ ፖለቲካዊ ተሳትፎ በመቀየር የመራጭነት ካርዳቸውን በንቃት በመውሰድ በዕድሉ እንዲጠቀሙ ያግዛል ነው ያሉት።


 

ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡም አስተያየት ሰጪዎቹ አረጋግጠዋል።

በባሌ ዞን በ5 የምርጫ ክልሎች ሥር በተደራጁ 537 የምርጫ ጣቢያዎች  የመራጮች ምዝገባ እየተከናወነ ሲሆን ኅብረተሰቡም በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ካርድ በመውሰድ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም