የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ለመምረጥ የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ እየወሰዱ ይገኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ለመምረጥ የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ እየወሰዱ ይገኛሉ
ሀዋሳ ፤መጋቢት 9/2018 (ኢዜአ)፡-የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች በጠቅላላ ምርጫው ለመምረጥ የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡
በምርጫ ሂደቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፉክክር ለማድረግ የሚያስችል ዝግጁነት ላይ እንገኛለን- ተፎካካሪ ፓርቲዎች
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሔደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ ነው፡፡
የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎችም በጠቅላላ ምርጫው ለመሳተፍና ለመምረጥ የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡
በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደገለጹት ምርጫ ዜጎች መብታቸውን በመጠቀም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሚናቸውን የሚወጡበት ዕድል በመሆኑ ተመዝግበው ለመምረጥ የሚያስችላቸውን ካርድ ወስደዋል፡፡
ከከተማው ነዋሪዎች መካከል የውቅሮ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ተገኝ በቀለ ባለፉት ጊዜያት በተካሄዱ ምርጫዎች እንደተሳተፉና ለዘንድሮ ምርጫም ካርድ ወስደው መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡
ምርጫ ዜጎች መብታቸውን ተጠቅመው ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሚናቸውን የሚወጡበት እድል ነው ብለዋል።
በመሆኑም ቤተሰቦቻቸውና የአካባቢያቸው ነዋሪዎች በምርጫው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እየቀሰቀሱ መሆኑን የገለጹት አቶ ተገኝ በመገናኛ ብዙሃን የሚደረግ የፓርቲዎችን ክርክር እንደሚከታተሉ ተናግረዋል፡፡
የዘንድሮ የምርጫ ሂደት በቴክኖሎጂ መታገዙ ዴሞክራሲያዊ ምርጫን ለማካሄድ ያግዛል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።
በተለይ ወጣቱ የምርጫ ተሳትፎውን ማጠናከር እንዳለበት የጠቀሱት አቶ ተገኝ፣ ሃገርን በተሻለ መምራት የሚችል ፓርቲን በእውቀት ላይ ተመስርቶ መምረጥ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመምረጥ እንደተዘጋጀች የገለጸችው ወጣት ፍሬህይወት ኪሮስ በበኩሏ የምርጫ ካርድ ወስዳ የተሻለ ሀሳብ ያለውን ፓርቲ ለመለየት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ክርክር እየተከታተለች መሆኗን ተናግራለች።
ለሴቶች ተጠቃሚነት የተሻለ ሀሳብ ያለውን ፓርቲ እንደምትመርጥና ሴቶችም በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው ተናግራለች።
በሚኖሩበት አካባቢ ዜጎች በምርጫው ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ድርሻቸውን እንዲወጡ በመቀስቀስ እየተሳተፉ መሆኑን የገለጹት አቶ ግርማ የማነህ ናቸው፡፡
በቀደሙት ምርጫዎች የተለያየ ተሳትፎ እንደነበራቸው ገልጸው በመራጭነት መሳተፍ የዜግነት ግዴታም ጭምር ነው ብለዋል፡፡
ለመምረጥ የሚያስችላቸውን ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸው የፖለቲካ ፓርቲዎች እየደረጉት ያለው ክርክርም ህዝቡ የተሻለውን ፓርቲ ለይቶ እንዲመርጥ እድል እየፈጠረ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።