የተለያዩ ተቋማት በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የተለያዩ ተቋማት በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ
አርባ ምንጭ ፤መጋቢት 9/2018 (ኢዜአ)፦በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች በተለያዩ ተቋማት ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የምግብ፣ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ፡፡
የገጠመንን ችግር በመጋራት መንግስትና ህዝቡ ላደረጉልን ድጋፍና ላሳዩን ሰብዓዊነት እናመሰግናለን
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከተለያዩ አካላትና ግለሰቦች የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በዛሬው እለትም የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ በዲላ ከተማ የሚገኙ 11 የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴክተር ተቋማት ሠራተኞች፣ የጋሞ ዞን ፖሊስ እና የአቢሲኒያ ባንክ ሀዋሳ ዲስትሪክት በአርባ ምንጭ ከተማ ተገኝተው የምግብ፣ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በአደጋው ለተጎዱ ወገኖች የ500 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡
የተቋሙ ዋና እንባ ጠባቂ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ፤ አደጋው የሁሉንም ልብ የሚሰብር መሆኑን ገልጸው፣ ተጎጂ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።
በተመሳሳይ በዲላ ከተማ የሚገኙ 11 የክልል ሴክተር ተቋማት ሠራተኞች 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።
ድጋፉን ያስረከቡት በክልሉ የዲላ ክላስተር ማስተባበሪያ አማካሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበባየሁ ኢሳያስ እንደገለፁት፤ በጋሞ ዞን በወገኖች ላይ የደረሰው አደጋ የሁሉንም ልብ የሰበረ ነው።
በዛሬው እለት የሴክተር ተቋማት ሠራተኞች ያደረጉት ድጋፍ ለእለት ደራሽ የሚሆን ምግብና አልባሳት ያካተተ መሆኑንም አስረድተዋል።
የጋሞ ዞን ፖሊስም 221 ሺህ ብር የሚገመት የዓይነት ድጋፍ እና 100ሺህ ብር ገንዘብ ለግሷል።
በዞኑ የሚገኙ የፖሊስ አባላትና አመራሮች በማዋጣት ያደረጉት ድጋፍ መሆኑን የጋሞ ዞን ፖሊስ አዛዠ ኢንስፔክተር አብርሃም ቡሄ ድጋፉን ሲያስረክቡ ገልጸዋል።
የዞኑ ፖሊስ አደጋው ከደረሰበት ዕለት ጀምሮ በነፍስ አድን ሥራዎችና ሌሎች ተግባራት ላይ ተሰማርቶ ሲያገለግል መቆየቱን አስታውሰው፣ በቀጣይ ወገኖችን ለማቋቋም በሚደረገው ጥረትም የበኩሉን ይወጣል ብለዋል።
የአቢሲኒያ ባንክ ሀዋሳ ዲስትሪክትና በሥሩ ያሉ ቅርንጫፎችም እንዲሁ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።
የዲስትሪክቱ ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ቦቸሬ ድጋፉን ሲያስረክቡ እንደገለጹት፤ በወገኖች ላይ የደረሰው ጉዳት ልብ ሰባሪ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዲስትሪክቱ እንዲሁም በሥሩ ባሉ ቅርንጫፎች ያሉ አመራሮችና ሠራተኞች ከደመወዛቸው በማዋጣት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ ማድርጋቸውን ተናግረዋል።
በዛሬው እለት ድጋፍ ያደረጉት ተቋማት በቀጣይ ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ርብርብም ድጋፋቸውን በማጠናከር ማህበራዊ ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
የጋሞ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ፤ በወገኖች ላይ በደረሰ አስከፊ አደጋና መሪር ሀዘን ወቅት ከጎናቸው የቆሙ አካላትን ሁሉ አመስግነዋል።
አደጋው ከደረሰበት ዕለት ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን አመራሮች እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ልሆኑ ተቋማትና ግለሰቦች ሀዘናቸውንና ድጋፋቸውን መግለጻቸውን አስታውሰዋል።
በዛሬው ዕለትም የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሐብታሙ ተገኝ ወደ ቦታው በማቅናት በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ቤተሰቦች በማጽናናት በተከሰተው የዜጎች ህይወት መጥፋት የተሰማቸውን ሐዘን ገልፀዋል።