በምርጫ ሂደቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፉክክር ለማድረግ የሚያስችል ዝግጁነት ላይ እንገኛለን- ተፎካካሪ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫ ሂደቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፉክክር ለማድረግ የሚያስችል ዝግጁነት ላይ እንገኛለን- ተፎካካሪ ፓርቲዎች
ባህር ዳር፤ መጋቢት 9/2018 (ኢዜአ)፡- በምርጫ ሂደቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፉክክር ለማድረግ የሚያስችል ዝግጁነት ላይ መሆናቸውን በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
በኢትዮጵያ ለ7ኛ ጊዜ ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የፓርቲዎች የክርክር መድረኮች በተለያዩ ሚዲያዎች በመካሄድ ላይ ሲሆን መራጮችም ድምፃቸውን ለመስጠት የሚያስችላቸውን ካርድ በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።
የምርጫ፤ ሂደት ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊነቱ የሚታየው በሂደቱ በመሆኑ ፓርቲዎች በነፃነት ሃሳባቸውን እያራመዱ ፖሊሲና ስትሬቴጂያቸውን ለህዝብ እያስተዋወቁ ቀጥለዋል።
ለሀገርና ህዝብ ሊጠቅም ይችላል የሚለውን ፓርቲ ለመምረጥም ዜጎች የፓርቲዎችን ሃሳቦች በመከታተል እየመዘኑ ስለመሆኑ ይናገራሉ።
በመሆኑም አጠቃላይ የምርጫውን ሂደትና ዝግጁነታቸውን በተመለከተ የኢዜአ ሪፖርተር በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን አነጋግሯል።
ጠቅላላ ምርጫውን ለማካሄድ ያሉ አስቻይ ሁኔታዎችን በመጠቀም ፖሊሲና ስትራቴጂያቸውን እንዲሁም ማንፌስቷቸውን ለህዝብ በማስተዋወቅ ለፉክከሩ መቅረባቸውን ገልጸዋል።
የፓርቲ አመራሮቹ በምርጫ ሂደቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፉክክር ለማድረግ የሚያስችል ዝግጁነት ላይ እንገኛለን እስከ ፍፃሜው ድረስም አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እመቤት ከበደ፤ ፓርቲያቸው በምርጫው ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ከማስተዋወቅ ባለፈ የበቁና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን እጩዎችን ማቅረቡን አንስተዋል።
አብን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሰላማዊ ትግል አራማጅ ፓርቲ መሆኑን አንስተው፤ በምርጫ ሂደቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፉክክር ለማድረግ የሚያስችል ዝግጁነት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የአማራ ዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ንቅናቄ (አዲሃን) ስራ አስፈፃሚ አባል አዲሱ ጉልላት፤ በዘንድሮው ምርጫ የምርጫ ህግና ደንቡን በማክበር ለመፎካከርና ኢትዮጵያን አሸናፊ ለማድረግ እየሰራን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም የፓርቲውን ፖሊሲና ፕሮግራሞች ለመራጩ ህዝብ የማስተዋወቅ ስራ በትኩረት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
በኢትዮጰያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የባህር ዳር ምርጫ ወረዳ አስተባባሪ ሃይለማርያም ብርሃኑ፤ በምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፉክክር በማድረግ ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ አሻራችንን ለማኖር እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
በፓርቲው የተዘጋጁ አማራጭ ፖሊሲዎችን እንዲሁም እጩዎችን ለመራጩ ህዝብ በማቅረብ የማስተዋወቅ ስራ እየሰራን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል።
በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው ምርጫ የመራጮች ምዝገባና ሌሎች የቅድመ ምርጫ ተግባራት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መርሃ ግብር መሰረት እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።