የገጠመንን ችግር በመጋራት መንግስትና ህዝቡ ላደረጉልን ድጋፍና ላሳዩን ሰብዓዊነት እናመሰግናለን - ኢዜአ አማርኛ
የገጠመንን ችግር በመጋራት መንግስትና ህዝቡ ላደረጉልን ድጋፍና ላሳዩን ሰብዓዊነት እናመሰግናለን
አርባ ምንጭ ፤መጋቢት 9/2018 (ኢዜአ)፡- የገጠመንን ችግርና ሀዘን በመጋራት ከጎናችን በመሆን መንግስትና አጠቃላይ ህዝቡ ላደረጉልን ድጋፍና ላሳዩን ሰብዓዊነት እናመሰግናለን ሲሉ በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ገለፁ።
በደቡብ ኢትዮጵያ በጋሞ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በጣለው ከባድ ዝናብ የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋ ተከስቶ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱ ይታወቃል።
በመሆኑም በአደጋው ሳቢያ ህይወታቸውን ያጡ ቤተሰቦችን የማፅናናት እና ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
የአደጋውን ተጎጂዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ሌሎችም የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ተቋማትና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በስፍራው በመገኘት አፅናንተዋል።
ከዚህም ባለፈ ለተጎጂዎችም የእለት ደራሽ ድጋፍና በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችል የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል።
የድጋፍ ስራውንና አጠቃላይ የአደጋው ሰለባዎች ያሉበትን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ የኢዜአ ሪፖርተር በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ ማዞ ዶይሳ ቀበሌ በመገኘት ተጎጂዎችን አነጋግሯል።
ከተጎጂዎቹ መካከል ወጣት እቴነሽ ኤራ፣ የደረሰብን ድንገተኛ አደጋ አስደንጋጭ ከመሆኑም ባለፈ ከፍተኛ ሀዘን ላይ ጥሎን አልፏል ብላለች።
አደጋው ወላጅ እናቷን ጨምሮ አጠቃላይ ቤት ንብረት ያሳጣት መሆኑን አንስታ ብዙዎች ከጎናችን በመሆን ፍቅርና ድጋፍቸው ስላልተለየን እየተፅናናን እንገኛለን ብላለች።
አሁን ላይ የእለት ደራሽ ምግብ፣ አልባሳትና ጊዜያዊ ማቆያ ስለተዘጋጀልን ማረፊያ አግኝተናል ብላለች።
በወረዳው የማዘ ዶይሳ ቀበሌ ነዋሪ አንተነህ አማቼ፣ እናቱንና ታላቅ ወንድሙን በአደጋው መነጠቁን ገልፆ ሀዘኑ የከፋ ቢሆንም በወገኖቻችን ጥረት እየተፅናናን እንገኛለን ብሏል።
በመንግስትና በዜጎች ልግስና ምግብ አልባሳትና ጊዜያዊ ማረፊያ አግኝተናል በማለት ለሁሉም ምስጋናውን አቅርቧል።
የደረሰው አደጋና ያስከተለው ጉዳት ከፍተኛ ቢሆንም መንግስትና ህዝቡ ከጎናችን በመሆኑ እየተፅናናን እንገኛለንም ብሏል።
ሌላኛው የአደጋው ሰለባ የሆኑት አቶ ገዙሜ ጉንታሴ፣ የደረሰው ድንገተኛ አደጋ ቤተሰብ፣ ወዳጅ፣ ዘመድና ጓደኞቻችንን አሳጥቶናል ብለዋል።
የደረሰው ጉዳትና ያጋጠመን ችግር የከፋ ቢሆንም በወገኖቻችን ድጋፍና አብሮነት እየተፅናናን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል።
በመሆኑም የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ህዝቡ በድንገተኛ አደጋ የገጠመንን ችግርና ሀዘን በመጋራት ላደረጉልን ድጋፍና ሰብዓዊነት እናመሰግናለን ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራርና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ኮሚሽነር ወገኔ ብዙነህ፣ በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ከማፅናናት ባለፈ የእለት ድጋፎችና የማቋቋም ስራዎች በቅንጅት እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።
ለዚህም የተለያዩ ተቋማት፣ ባለሃብቱና አጠቃላይ ዜጎች እያደረጉት ላለው ድጋፍና እገዛ አመስግነው በዘላቂነት የማቋቋም ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።