በአስተዳደሩ የሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በላቀ መልኩ ሊወጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በአስተዳደሩ የሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በላቀ መልኩ ሊወጡ ይገባል
ድሬዳዋ፤ መጋቢት 9/2018(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ አሰተዳደር የሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በላቀ መልኩ ሊወጡ እንደሚገባ በአስተዳደሩ ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ኢብራሂም ዩሱፍ ገለጹ።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ የሚጠበቅብንን እንወጣለን-የፖለቲካ ፓርቲዎች
የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ለመገናኛ ብዙኃን እና ለማኅበራዊ ሚዲያ ባለሙያዎች በምርጫ ሥነ-ምግባር ዙሪያ የአቅም ግንባታ መድረክ አካሂዷል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ በአስተዳደሩ ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ኢብራሂም ዩሱፍ በወቅቱ እንዳሉት፤ ዘንድሮ የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።
ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ በማገዝ በኩል የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ትክክለኛ መረጃን በፍትሐዊነት ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
ሥልጠናውም ባለሙያዎች በዕውቀት በመታገዝ ሁሉንም አካላት በእኩልነት እንዲያገለግሉ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ብሩክ ወርቅነህ፤ የሚዲያ ባለሙያዎች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መዳበር የድርሻቸውን እንዲወጡ ሥልጠናው ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በምርጫ ወቅት ሙያዊ ሥነ-ምግባርን በመጠበቅ፣ ትክክለኛና ታማኝነተ ያለው መረጃን በፍጥነት ለሕዝብ ማድረስ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በሥልጠናው የተሳተፉ ጋዜጠኞች በበኩላቸው፤ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የምርጫ ሕግና ደንብን እንዲሁም ሙያዊ ሥነ-ምግባርን በማክበር በንቃት እንደሚሠሩም አስታውቀዋል።