ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ የሚጠበቅብንን እንወጣለን-የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ የሚጠበቅብንን እንወጣለን-የፖለቲካ ፓርቲዎች
አዲስ አበባ፤መጋቢት 9/2018 (ኢዜአ)፦ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ፡፡
ምርጫ ሀገርንና ህዝብን የሚመራ መንግስት መመስረት የሚያስችል ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ፣ ሂደቱ ነፃ፣ ፍትሀዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ሁሉም የሚጠበቅበትን ሊወጣ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ በምርጫ ጣቢያዎችና በበይነ-መረብ የመራጮች ምዝገባ በሂደት ላይ ይገኛል።
ይህንን ተከትሎ በመጪው ግንቦት ወር ለሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የምርጫ ስነ-ምግባር ደንቡን አክብረው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር እንደገለጹት፤ ምርጫ ለሀገር ግንባታና ዘላቂ ልማትን ወሳኝ እርምጃ ነው።
ፓርቲያቸው ምርጫው ስኬታማና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ከወዲሁ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ ምርጫው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማስፈን ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ነጻነት ጣሰው በበኩላቸው፥ የዘንድሮው ምርጫ በቴክኖሎጂ የታገዘ መሆኑን አድንቀው ፓርቲያቸውም የዕጩዎችን ምዝገባ በዚሁ መንገድ ማካሄዳቸውን ጠቅሰዋል።
የዘንድሮው ምርጫ ካለፉት ሂደቶች በተለየ መልኩ ታሪካዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፥በተለይም መርጫው ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር አክለውም፥ በዘንድሮው ምርጫ በነጻነት ለመወዳደር የሚያስችል ሰፊ ምህዳር መፈጠሩን አንስተዋል፡፡
ህዝቡ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ የመራጭነት ካርድ እንዲወስድም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።