የህብረተሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሰው ተኮር ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የህብረተሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሰው ተኮር ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤መጋቢት 9/2018 (ኢዜአ)፦ የህብረተሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሰው ተኮር ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ1447ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካሞች፣ አረጋውያን እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የማዕድ ማጋራት አከናውነዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ መረዳዳት የኢትዮጵያውያን የቆየ እሴት መሆኑን ጠቁመው፤ በበዓል ወቅት ካለን ላይ ለሌላቸው በማካፈል ደስታን መጋራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
ድጋፉ ከልበ ቀና የህብረተሰብ ክፍሎች እና ባለሃብቶች መገኘቱን ጠቁመው፤ ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የዒድ አል-ፈጥር በዓልን አስመልክቶ ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች ማዕድ አጋራ
በመዲናዋ ከወቅታዊ ድጋፍ በተጨማሪ ዘላቂነት ያላቸው በርካታ ሰው ተኮር ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸው እነዚህ ሰው ተኮር ተግባራትም የህብረተሰቡን ህይወት በማሻሻል ረገድ ተጨባጭ ለውጦች እየተመዘገቡባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ይመር ከበደ በበኩላቸው፤ ማዕድ ማጋራት በከተማዋ ባህል እየሆነ መጥቷል ብለዋል።
መርሃ ግብሩ ከማዕድ ማጋራት ባሻገር ወንድማማችነትንና የሰው ተኮር አስተሳሰብን በተግባር የገለጠ መሆኑን አመላክተዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በበኩላቸው፤ ድጋፉ በዓሉን በደስታ ለማሳለፍ እንደሚያግዛቸው ገልጸው ምስጋና አቅርበዋል።