ቀጥታ፡

ከተማ አስተዳደሩ የዒድ አል-ፈጥር በዓልን አስመልክቶ ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች ማዕድ አጋራ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 9/2018 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዒድ አል-ፈጥር በዓልን አስመልክቶ ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች ማዕድ ማጋራቱን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ፣ ለአቅመ ደካሞች፣ለአካል ጉዳተኞች ፣ እንዲሁም ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው የከተማችን ነዋሪዎች የሚደረገው ይህ የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር በሁሉም የከተማችን ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህ የረመዳን ወቅትም 27 ሺህ ያህል ወገኖቻችን ወሩን በሙሉ በ28ቱም የምገባ ማዕከሎቻችን የአፍጥር ፕሮግራም ተዘጋጅቶላቸው ያለ ችግር እንዲያሳልፉ ተደርጓል ብለዋል።


 

ከንቲባ አዳነች፥ የማዕድ ማጋራት የምናደርገው ጊዜያዊ ችግርን ለመቅረፍ ብቻ ሳይሆን ለሕዝባችን ያለንን ክብር ለመግለጽ ሲሆን፤ ወንድማማችነትን እና የእርስ በእርስ መደጋገፍ እሴትን ለማጎልበት ነዉ ያሉት።

እንደ ሁልጊዜውም በከተማችን በምናከናውናቸው የማዕድ ማጋራት ሥራዎች ላይ በማስተባበር፣ አቅመ ደካሞችን በጉልበታቸው በማገዝ ደፋ ቀና ለሚሉ የከተማችን ወጣቶችን፣ካላቸው ቆርሰው ለመስጠት ለማይሳሱ ባለሀብቶችና የከተማችን ነዋሪዎች በተጠቃሚዎች ስም አመሰግነዋል።


 

በተለይም ዛሬ በከንቲባ ጽሕፈት ቤት የተደረገው የማዕድ ማጋራት ለደገፉት ለሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለአቶ ጀማል አሕመድ እና የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ኤምባሲ ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም