ቀጥታ፡

የምርጫ ካርዳችንን በመያዝ የዜግነት ሃላፊነታችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል

ጎንደር ፤ መጋቢት 8/2018(ኢዜአ)፦ የምርጫ ካርዳችንን በመያዝ የዜግነት ሃላፊነታችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ በጎንደር ከተማ የምርጫ ካርድ ሲወስዱ ያገኘናቸው ነዋሪዎች ተናገሩ።

ወጣቶች በጠቅላላ ምርጫው ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ክርክሮች፣ የምርጫ ቅስቀሳ እንዲሁም ፖሊሲና ስትራቴጂያቸውን የማስተዋወቅ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በገጠርም ይሁን በከተሞች ዜጎች በኦን-ለይን እንዲሁም በየምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ለመምረጥ የሚያበቃቸውን የምርጫ ካርድ በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።

በዚህም መሰረት በጎንደር ከተማ በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ካርዳቸውን ሲወስዱ ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ካርዳችንን በመያዝ የዜግነት ሃላፊነታችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ብለዋል።


 

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል ወጣት ዮሃንስ ቼኮል፤ የምርጫ ሂደቱ እንግልት የሌለውና ቀልጣፋ አሰራርን የተከተለ መሆኑን አንስቶ ነገ ለምንወስንበት ወይም ድምፅ ለምንሰጥበት ዛሬ ላይ የምርጫ ካርድ መውሰድ የግድ ይለናል ብሏል።

በሀገራችን የዴሞክራሲ ስርአት እንዲገነባ በህዝብ የተመረጠ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ያስፈልጋል ያለው ወጣት ዮሃንስ በምርጫው የነቃ ተሳትፎ ማድረግ የሁላችንም ሃላፊነትና የዜግነት አደራችን ነው ብሏል።

በዚህም መሰረት በምርጫው እለት ድምጽ ለመስጠት የሚያስችለውን የምርጫ ካርድ በእጁ ማስገባቱን ገልፆ ሌሎች ወጣቶችም እድሉ ሊያመልጣቸው እንደማይገባ መልእክቱን አስተላልፏል።

ሌላኛዋ የምርጫ ካርድ ሲወስዱ ያገኘናቸው ወይዘሮ ፈንታነሽ ሙላት፤ በተለይም ለሴቶች እኩልነትና መብት መረጋገጥ ይሆነናል የምንለውን ፓርቲ በድምፃችን መወሰን ይገባናል ብለዋል።


 

ለዚህም ዛሬ ላይ የምንመርጥበትን ካርድ መውሰድ የግድ ይሆናል ያሉት ወይዘሮ ፈንታነሽ፤ ሴቶች ለምርጫና ለዴሞክራሲ ግንባታ ሚናችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

የቅድመና ድህረ ምርጫው ሂደትና ውጤቱ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊና በህዝብ ዘንድ ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅም  የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ የሺወርቅ ባያብል፤ በየአምስት አመቱ የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ሴቶች በምርጫው እኩል ተሳትፎ የሚያደርጉበትን የፖለቲካ ምህዳር የሚፈጥር ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የሴቶች ዴሞክራሲያዊ መብት ይበልጥ እየተጠናከረ የሚሄደው ሴቶች በመምረጥም ይሁን በመመረጥ ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ ሲችሉ ነው ብለዋል።

በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው ምርጫ የመራጮች ምዝገባና ሌሎች የቅድመ ምርጫ ተግባራት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መርሃ ግብር መሰረት እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም