ወጣቶች በጠቅላላ ምርጫው ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች በጠቅላላ ምርጫው ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ባህር ዳር፤ መጋቢት 7/2018 (ኢዜአ)፡-ወጣቶች በመጪው ጠቅላላ ምርጫ በመምረጥም ሆነ በመመረጥ ረገድ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የአማራ ክልል ወጣቶች ማህበራት ፌዴሬሽን አስታወቀ።
በጠቅላላ ምርጫው በንቃት በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው የበኩላችንን አስተዋፅኦ እናበረክታለን
የአማራ ክልል ወጣቶች ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወጣት ግርማ አቸነፍ ለኢዜአ እንደገለጸው፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እንደ ሲቪክ ማህበር የሚጠበቁ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ወጣቶች የምረጡኝ ቅስቀሳዎችን በትኩረት በመከታተል ይበጀኛል፤ ይጠቅመኛል ብለው ያመኑበትን ፓርቲ እንዲመርጡ የግንዛቤ ፈጠራ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው ብሏል።
ፌዴሬሽኑ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር የታዛቢነትና የአስተባባሪነት ህጋዊ ሰርቲፊኬት ወስዶ ወደ ተግባራዊ ስራ መግባቱንም አረጋግጧል።
መንግስትና ሃገር የሚፀናው በዲሞክራሲያዊ ምርጫ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ወጣቱ የምርጫ ካርድ በነቂስ እንዲያወጣ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስረድቷል።
ወጣቱ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን አማራጭ ሃሳብ መዝኖ የሚጠቅመውን ከመለየት ባለፈ ምርጫው ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ የግንዛቤ ማጎልበት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ወጣቱ ኃይል ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚኖረው ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቅሶ፤ የምርጫ ካርድ ከማውጣት ባለፈ ዘላቂ ሰላምና ልማት ያመጣልኛል የሚለውን ፓርቲ እንዲመርጥም አስገንዝቧል።
ወጣት ጥላሁን አበበ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ሲሆን በመጪው ምርጫ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ለመሆን ከወዲሁ ለመራጭነት የሚያበቃውን የምርጫ ካርድ መያዙን ገልጿል።
ምርጫው በማንኛውም መለኪያ ሰላማዊና አሳታፊ እንዲሆን የድርሻውን እንደሚወጣ ጠቁሞ፤ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸውን አማራጭ ፖሊሲዎች በማመዛዘን ለመምረጥ መዘጋጀቱን ተናግሯል።
በያዘችው የመራጭነት ካርድ የወጣቱን ፍላጎትና ጥያቄ በአግባቡ ተረድቶ ምላሽ ይሰጣል ብላ ላመነችበት ፓርቲ ድምጿን ለመስጠት መዘጋጀቷን የገለፀችው ደግሞ ወጣት ፋሲካ አማረ ናት።
ፓርቲዎች እያደረጉት ባለው የምረጡኝ ቅስቀሳ አማራጭ ፖሊሲዎቻቸውን ለመረዳት እንደቻለች ጠቅሳ፤ ይህም የተሻለ ጠቃሚ አጀንዳ ያለውን ለመለየት እንዳገዛት ተናግራለች።
ምርጫው ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የራሷን ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀቷንም አረጋግጣለች።