ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የዲጂታል ልማት ስትራቴጂ ለአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል መሰረት እየሆነ ነው

አምቦ ፤ መጋቢት 8/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የዲጂታል ልማት ስትራቴጂ ለሀገር ግንባታና ለአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል መሰረት መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።

በጎንደር ከተማ በዲጂታል የተደገፈ የአድራሻ ስርዓት ትግበራ ተጀመረ

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የሀገሪቱን የቴክኖሎጂ ልማት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል ርእይ ተሰንቆ የተበሰረ ግዙፍ የልማት እቅድ መሆኑ ይታወቃል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ራዕይ "በፈጠራ የታገዘች፣ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠ እና አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ የገነባች ኢትዮጵያን ማየት" ነው።

እቅዱ የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" ስኬቶችን መሠረት በማድረግ በቀጣይ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ማዕከል የማድረግ ትልም የሰነቀ ነው።

በዚህም መሰረት በተቀናጀ መልኩ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ሲሆን መንግስት በዘርፉ ልማት የኤአይ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ሌሎች እቅዶችን ለማሳካት እየሰራ ይገኛል።

በስትራቴጂክ እቅዱ መሰረትም የዜጎችን የዲጂታል አቅም በማጎልበት የተቋማት አሰራር ይበልጥ ዘመናዊ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ እንዲሆን ማድረግ ዋነኛው ትኩረት ነው።

የሥራ ዕድል መፍጠር፣ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ድርጅቶችን ስታርት አፖች ማበረታታት እና ቁልፍ የምጣኔ ሃብት ሴክተሮችን ማዘመንም ሌላኛው ትኩረት መሆኑ ይታወቃል።

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁራን ለኢዜአ እንደገለጹት፤  የኢትዮጵያ የዲጂታል ልማት ስትራቴጂ ለሀገር ግንባታና ለአገልግሎት መሻሻል መሰረት መሆኑንና ለእቅዱ ስኬት የሁሉም ጥረት ወሳኝ ነው።

ከምሁራኑ መካከል በዩኒቨርሲቲው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ናኦል በቀለ (ዶ/ር)፤ እንደገለጹት በኢትዮጵያ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ዲጂታል ማድረግ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው።


 

በተለይ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ መተግበሩን ተከትሎ በፋይናንስ፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በሌሎችም ዘርፎች የተገኙት እድገቶች የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።

"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ ደግሞ በኢኮኖሚ፣ በመንግሥታዊ አስተዳደርና በማኅበራዊ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት ያለመ በመሆኑ ለስኬታማነቱ መንግስትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት አገልግሎታቸውን ይበልጥ ዲጂታላይዝ  በማድረግ ሊረባረቡ እንደሚገባ አስረድተዋል።

ዲጂታል ኢትዮጵያ የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን የዜጎችን ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባለፈ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ከብልሹ አሰራሮች የጸዱ በማድረግ የተገልጋይ እርካታን ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።

እንዲሁም ስትራቴጂው በሁሉም ዘርፎች የዜጎችን አካታችነትና አሳታፊነትን በማረጋገጥ የሀገሪቱን እድገት ለማፋጠን እንደሚያስችልም አብራርተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የኔትዎርክ አስተዳደር ቡድን መሪ ኩማራ በቀለ በበኩላቸው፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት አሰጣጥን ከማስፋፋት ባለፈ የዜጎችን ተወዳዳሪነት አቅም እንደሚያሳድግ ገልጸዋል።

በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ለዜጎች መሰጠቱ ጊዜ፣ ጉልበት እና ሀብት አላግባብ ሳይባክን ለታለመለት ዓለማ እንዲውል ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

እንዲሁም ሀገሪቱ የጀመረቻቸው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ በማጠናቀቅ ከአደጉ አገራት ተርታ እንድትሰለፍ ያደርጋታል ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የያዘችው የ2030 የዲጂታል ስትራቴጂ እንዲሳካ የዘርፉ ምሁራን በአካባቢያቸው፣ በክልልና በፌዴራል ደረጃ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ የሚስተዋሉ የእውቅት ክፍተቶችን በመሙላት ለዜጎች አስፈላጊውን ግንዛቤ በማስጨበጥ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም