ቀጥታ፡

በጎንደር ከተማ በዲጂታል የተደገፈ የአድራሻ ስርዓት ትግበራ ተጀመረ

ጎንደር፤ መጋቢት 7/2018 (ኢዜአ)፡- በጎንደር ከተማ የዲጂታል የአድራሻ ስርዓት ትግበራ መጀመሩን የከተማ አስተዳደሩ ስማርቲ ሲቲ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬተር ይልቃል ሙሉአለም (ዶ/ር ) ለኢዜአ እንደተናገሩት በቴክኖሎጂው የትግበራ ሂደት በከተማው ለሚገኙ 1 ሺ 500 የመኖሪያና የንግድ ተቋማት ዲጂታል የቤት ቁጥር መስጠት ተጀምሯል፡፡

የዲጂታል አድራሻ ስርአቱ ነዋሪዎች የቤት መለያ ቁጥራቸውን ብቻ በማሳወቅ የአንቡላንስና የእሳት አደጋ ጥሪዎችን ጨምሮ የውሃ፣ የቴሌና የመብራት የጥገና አገልግሎቶችን በቤታቸው ሆነው የሚያገኙበት የዲጂታል የአሰራር ስርአት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የከተማውን የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶች በዲጂታል አድራሻ ስርአቱ በመታገዝ የቱሪዝም ስፍራዎችን የመዝናኛና ማረፊያ ሆቴሎችን በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ ቴክኖሎጂው ይበልጥ አጋዥ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በከተማው የመሬት አስተዳደር ስርአቱን በዲጂታል ማዘመን እንዲቻል በተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችም በአሁኑ ወቅት ከ600 ሽህ በላይ የመሬት ይዞታ መረጃዎችን ዲጂታላይዝ በማድረግ ወደ ሲስተም የማስገባት ስራ ተከኗውኗል ብለዋል፡፡

የከተማው የመሬት አስተዳደር ስርአት ዲጂታላይዝ በመደረጉም በአሁኑ ወቅት የቤትና የቦታ ባለይዞታዎች የዲጂታል ካርታ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዘመናዊ አሰራር መዘርጋት እንደተቻለም አብራርተዋል፡፡  

የዲጂታል ካርታ አሰራር መጀመሩ በዘርፉ ይታይ የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የመሬት ወረራንና ብልሹ አሰራርን ከመሰረቱ ለመቅረፍ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡  

የከተማው ገቢዎች፣ የንግድና ገበያ ልማት መምሪያዎችም ወደ ዘመናዊ ዲጂታል የአገልግሎት አሰጣጥ ስርአት የሚሸጋገሩበትን ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በከተማው መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎትን ለመጀመር ግንባታው እየተፋጠነ ለሚገኘው የማእከሉ ህንጻም የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን የመዘርጋት ስራ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡ 

በማእከሉ ለተመደቡ ሰራተኞችም የዲጂታል አውቅትና ክህሎታቸውን ለማሳደግ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ሀገር የተጀመረው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ኢንሼቲቭ በዲጂታል ቴክኖሎጂው ዘርፍ እመርታዊ ለውጥና እድገት ለማስመዝገብ  አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ የዲጂታል አድራሻ ስርአት ትግበራውን እያከናወነ የሚገኘው ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር እንደሆነም አመልክተዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም