ቀጥታ፡

የሰላም ሚኒስቴር በጋሞ ዞን የተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የ3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ 

‎አርባ ምንጭ ፤ መጋቢት 8/2018(ኢዜአ)፦ የሰላም ሚኒስቴር በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የ3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ። 

በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የሚደረጉ ሰብዓዊ ድጋፎች ተጠናክረው ቀጥለዋል

የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ፤ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት ባስተላለፉት መልእክት ወገኖች ከደረሰባቸው ጉዳት እንዲጽናኑ መንግስትና ህዝቡ በቅርበት እየደገፈ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም መሰረት የሰላም ሚኒስቴር ለአደጋው ተጎጂዎች አሁን ላይ የ3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።


 

ወገኖቻችንን በዘላቂነት ለማቋቋም ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ሚኒስትሩ በመተባበርና በመደጋገፍ ችግሮችን ማለፍ ይኖርብናል ብለዋል።

‎በተመሳሳይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት፣ ቱሪዝም ቢሮ እና ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ በጋራ የ300 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል።

‎የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ  ደምሴ አድማሱ (ዶ/ር) ድጋፍ እያደረጉ ላሉ ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋና አቅርበዋል።


 

‎አደጋው ከደረሰበት ዕለት ጀምሮ የመንግስት አካላት፣ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች ተጎጂዎችን በመደገፍና በማፅናናት ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የዕለት ደራሽ ድጋፍ ስራው እንዳለ ሆኖ በአስተዳደሩ በኩል በዘላቂነት የማቋቋም ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው በዚህ ተግባር ከተጎጂዎች ጎን የቆሙ ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም