በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የሚደረጉ ሰብዓዊ ድጋፎች ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የሚደረጉ ሰብዓዊ ድጋፎች ተጠናክረው ቀጥለዋል
አርባ ምንጭ ፤ መጋቢት 8/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች በተለያዩ አካላት የሚደረጉ ሰብአዊ ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የጋሞ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።
በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ ከማድረግ ጎን ለጎን መልሶ ለማቋቋም በቅንጅት እየተሰራ ነው
በትናንትናው ዕለትም የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የዓይነትና የገንዘብ ድጋፎችን አድርገዋል።
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች በደረሰው አደጋ በሰዎች ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።
አደጋው ከደረሰበት ዕለት ጀምሮ የፌዴራልና የክልል መንግስት አካላት፣ የዞን፣ የከተማና ወረዳ አስተዳደሮች እንዲሁም የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ግለሰቦች ሀዘናቸውን በመግለፅ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ድጋፉ ተጠናክሮ በመቀጠል በትናንትናው እለትም የተለያዩ አካላት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው፣ ህብረተሰቡ ለጋሞ ህዝብ ላሳየው ወንድማዊ ፍቅርና ድጋፍ አመስግነዋል።
በአርባ ምንጭ ከተማ ተገኝተው ድጋፍ ካደረጉት መካከል የአሪ ዞን አንዱ ሲሆን የዞኑን ህዝብና አስተዳደር ወክለው ድጋፉን ያስረከቡት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሀም አታ እና ሌሎች አመራሮች ናቸው።
አስተዳዳሪው በዚህ ውቅት እንደገለጹት፤ በጋሞ ዞን በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ የብዙዎች ሕይወት በመቀጠፉ የዞኑ አስተዳደርና ህዝብ በእጅጉ አዝነዋል።
በዚህም በትናንትናው እለት የ500 ሺህ ብር ግምት ያላቸው የምግብ እና የተለያዩ ቁሳቁስ ድጋፍ ይዘው በመምጣት ማስረከባቸውን አስረድተዋል።
በቀጣይም የአሪ ዞን አስተዳደርና ህዝብ ከጋሞ ህዝብ ጎን ይቆማል ሲሉም አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ የኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ግሩፕ ግምታቸው አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የምግብና የአልባሳት ድጋፍ አድርጓል፡፡
ግሩፑን በመወከል ድጋፉን ያስረከቡት የኃይሌ ሪዞርት አርባ ምንጭ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት ታሪኩ፣ በወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጉዳት የድርጅቱን ሠራተኞችና አመራሩን በእጅጉ ያሳዘነ ነው ብለዋል።
ያደረጉት ድጋፍ ለአስቸኳይ ጊዜ ሰብዐዊ እርዳታ የሚሆንና ግምቱ አንድ ሚሊዮን ብር እንደሚገመት ጠቅሰው፣ በቀጣይም ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ የሚደረገው ድጋፍ ይጠናከራል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንም እንዲሁ የ200 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጥላሁን ብርሀኑ፤ በወገኖቻችን ላይ በደረሰው አስከፊ አደጋ የኮርፖሬሽኑ አመራሮችና ባለሙያዎች እጅግ አዝነናል ብለዋል፡፡
የገንዘብ ድጋፉ እንደመጀመሪያ የተደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይም ተጎጂዎች ተቋቁመው ወደ መደበኛ ህይወታቸው እስኪመለሱ ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በተመሳሳይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ እንዲሁም የአርባ ምንጭ ቱሪስት ሆቴል ከ600 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።
የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ካሠች ኤልያስ፤ የመሬት መንሸራተት አደጋ ባስከተለው ሰብአዊና ቁሳዊ ሀብት ውድመት ማዘናቸውን ገልጸዋል።
በአደጋው የተፈናቀሉ ህፃናት፣ ነፍሰ ጡር ሴቶች እና አቅመ ደካሞችን በልዩ ሁኔታ ድጋፍ ለማድረግ የመለየት ሥራ መከናወኑንም ጠቁመዋል፡፡
አርባ ምንጭ ቱሪስት ሆቴል ተወካይ አቶ አበበ ንጋቱ በበኩላቸው፤ ለተጎዱ ወገኖች በእጅጉ እንዳዘኑና መልሶ በመቋቋሙ ሂደት ሆቴሉ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።