ቀጥታ፡

በምስራቅ ጎጃም ዞን ከ970 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመንገድ ግንባታና ጥገና ተከናውኗል

ደብረ ማርቆስ፤ መጋቢት 7/2018 (ኢዜአ)፡- በምስራቅ ጎጃም ዞን ባለፉት ስምንት ወራት ከ970 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የአዲስ መንገድ ግንባታ፣ ጥገና እና ተያያዥ ተግባራት መከናወናቸውን የዞኑ መንገድ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ መምሪያ አስታወቀ።

የኮሪደር ልማት ዘመናዊ ከተሜነትን በማስፋፋት ከተሞችን የብልጽግና ማዕከል እያደረገ ነው

መምሪያው ባለፉት ስምንት ወራት የተከናወኑ ተግባራትን የሚገመግም መድረክ በደብረ ማርቆስ ከተማ አካሂዷል። 

በመድረኩ ላይ የመምሪያው ኃላፊ አቶ ማናየ አዳነ እንደገለጹት፤ የመንገድና ትራንስፖርት ዘርፉ ለአገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ለማህበራዊ ትስስር የጀርባ አጥንት መሆኑን በመገንዘብ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

በዚህም ከመንግስት፣ ከረድኤት ድርጅቶችና ከማህበረሰቡ በተገኘ ከ970 ሚሊየን ብር በላይ በጀት የተለያዩ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

ከተከናወኑ ተግባራት መካከል 652 ኪሎ ሜትር መንገድ የጥገና ሥራ፣ ከ11 ኪሎ ሜትር በላይ አዲስ የጠጠር መንገድ ግንባታ እና 30 ኪሎ ሜትር የውሃ ማፋሰሻ ቦይና ሌሎች ግንባታና ጥገና መካሄዱን ገልጸዋል።

እነዚህ የግንባታና የጥገና ሥራዎች በጎዛምን፣ በማቻከል፣ በደብረ ኤሊያስ፣ በሰዴ፣ በባሶ ሊበንና በሌሎችም ወረዳዎች መከናወናቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል።


 

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ዋለ አባተ በበኩላቸው፤ መንግስት ህብረተሰቡንና ባለሀብቶችን በማስተባበር ለመሠረተ ልማት ዝርጋታ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል። 

በተለይም በትራንስፖርት ስምሪት ላይ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችንና ሙስናን ለማስወገድ የዲጂታል አሰራርን መተግበር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በፌዴራልና በክልል መንግስት ድጋፍ ተጨማሪ የ200 ኪሎ ሜትር መንገድና የሰባት ድልድዮች ግንባታ በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም