ተማሪዎችን በእውቀትና በሥነ ምግባር የማነጽ ግንባር ቀደም ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው-የጎንደር ከተማ መምህራን - ኢዜአ አማርኛ
ተማሪዎችን በእውቀትና በሥነ ምግባር የማነጽ ግንባር ቀደም ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው-የጎንደር ከተማ መምህራን
ጎንደር ፤ መጋቢት 7/2018 (ኢዜአ)፦ተማሪዎችን በእውቀትና በሥነ ምግባር የማነጽ ግንባር ቀደም ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ በጎንደር ከተማ የሚገኙ መምህራን ገለጹ፡፡
ሴቶች ጠንክረን ከሰራን በማንኛውም መስክ ስኬታማ መሆን እንችላለን-ተመራቂ የሕክምና ባለሙያዎች
የአማራ ክልልና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች "ለሰላም ዘብ እቆማለሁ፤ የልማት አርበኛ እሆናለሁ" በሚል መሪ ሀሳብ ከከተማዋ መምህራን ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል መምህር ብሩክ አንዳርጌ እንደገለጹት፤ በእውቀት የተገነባና በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ በማፍራት በኩል የመምህራን ተሳትፎና ጥረት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
መምህራን የእውቀት አባት እንደመሆናችን ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ትኩረት በመስጠት በእውቀትና በስነምግባር የታነጻ ዜጋ ለማፍራት በቁርጠኝነት እየሰራን እንገኛለን ሲሉ ገልጸዋል።
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ መምህር ታድሎ ጸጋ በበኩላቸው፤ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲኖር ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ለአካባቢው ሰላም መጠናከር ከመንግስት ጋር በመተባበር እንሰራለን ብለዋል።
"የሰው ሃብት ልማት ለአንድ ሀገር እድገት መፋጠን አበርክቶው ከፍተኛ ነው" ያሉት መምህር ታድሎ ይህንን ለማሳካት በትምህርት ጥራት፣ አግባብነትና ተደራሽነት ላይ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በትውልድ ግንባታና ቀረጻ ላይ የመምህራንና የትምህርት ቤቶች ሚና የጎላ መሆኑን የገለጹት ደግሞ መምህር ሰለሞን ታደለ ናቸው፡፡
ተማሪዎች ነገ ለሀገርና ለህዝብ ጠቃሚ እንዲሆኑ በትምህርት ቆይታቸው በቂ እውቀትና ክህሎት በማስጨበጥ ሀላፊነታቸውን ለመወጣት እየሰሩ መሆኑንም አስረድተዋል።
መንግስት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻልና የትምህርት ግብአቶችን በማሟላት በኩል እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበትም ነው የገለጹት።
የአማራ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ/ር) በመድረኩ እንደገለጹት፤ በክልሉ የሰፈነው ሰላም ከትምህርት ገበታ ተለይተው የቆዩ በርካታ ህጻናትን ወደ ትምህርት ለመመለስ አስችሏል።
የመማር ማስተማር ስራው ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲከናወን መምህራን ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ሰላምን ማስቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ፣ የተማሪዎችን ውጤት በማሻሻልና ምቹ የመማር ማስተማር አካባቢን በመፍጠር ረገድ ውጤት ተመዝግቧል ያሉት ደግሞ የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ናቸው፡፡
ከደረጃ በታች የሆኑ ትምህርት ቤቶችን በአዲስ በመገንባት፣ የትምህርት ግብአቶችን በማሟላትና የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር በማካሄድ ውጤታማ ተግባር ለማከናወን መቻሉን አስረድተዋል፡፡
የዛሬው የውይይት መድረክ ዓላማም የከተማው ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የልማት እቅዶችም እንዲሳኩ በማድረግ በኩል መምህራን የነበራቸውን የላቀ ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥል ለማስቻል ነው ብለዋል።
በመድረኩ ላይ ከጎንደር ከተማ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ርዕሰ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮችና መምህራንን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ የትምህርት አመራሮች ተሳትፈዋል።