ቀጥታ፡

ሴቶች ጠንክረን ከሰራን በማንኛውም መስክ ስኬታማ መሆን እንችላለን-ተመራቂ የሕክምና ባለሙያዎች

አዲስ አበባ፤መጋቢት 6/2018 (ኢዜአ)፡-ሴቶች ጠንክረን ከሰራን ፈተናዎችን በጽናት በማሸነፍ በማንኛውም መስክ ስኬታማ መሆን እንችላለን ሲሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለ54ኛ ዙር ተመራቂ የሕክምና ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለ54ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 263 የሕክምና ተማሪዎችን በትናንትናው ዕለት ያስመረቀ ሲሆን፤ 120 የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙ ሴት ተመራቂዎች "ሴቶች ጠንክረን ከሰራን በማንኛውም መስክ ስኬታማ መሆን እንችላለን" ሲሉ ገልጸዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ሴት የሕክምና ባለሙያዎች፣የሕክምና ትምህርት ያለውን ፈታኝ ባህሪ ተቋቁመው ለዚህ ማዕረግ በመብቃታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

የሕክምና ሙያ በሚጠይቀው መሠረትም በፍቅር፣ በርኅራኄና ሥነ-ምግባር በተላበሰ መልኩ ሕዝባቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

ተመራቂ ዶክተር ሲሃም ጀማል፤ሴቶች ጠንክረው ከሰሩ በማንኛውም ሙያ ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ በተግባር አሳይተናል በማለት ምስክርነቷን ሰጥታለች።

የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚዋ ዶክተር ሜሮን ለገሰ በበኩሏ፤ "ሴቶች ጠንክረን ከሰራን ያለምነውን ከማሳካት የሚያግደን ምንም ነገር የለም" በማለት የሴቶች ከፍተኛ ውጤት አስመዝጋቢነትን በምሳሌነት አንስታለች።


 

የተለያዩ ውጣ ውረዶችን በማለፍ ስኬታማ መሆን እንደሚቻል የገለጸችው ዶክተር ቤተል አማኑኤል፤ሙያው በሚጠይቀው መሠረት በፍቅር፣ በርህራሄና በሥነ-ምግባር ሕዝባቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጣለች።


 

ተመራቂዎቹ በቆይታቸው ያካበቱትን ዕውቀትና ክህሎት በመጠቀም፣ የጤናውን ዘርፍ ለማገዝ ከፍተኛ ተነሳሽነት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

የኮሌጁ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶክተር ራሄል አርጋው በቅድመ-ምረቃ መርሃ ግብር 60 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ገልጸው፤ተቋሙ የላቀ ችሎታ ያላቸውን ሴት ባለሙያዎች በማፍራት ረገድ ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በዕለቱ ከተመረቁት መካከል የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚዋን ጨምሮ ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ የያዙት ሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሴቶች በዚህ ደረጃ ውጤታማ መሆን ለቀጣይ ትውልድ ሴት ተማሪዎች ትልቅ መነሳሳትን እንደሚፈጥርም በመርሃ ግብሩ ላይ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም