የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ነጠላ የኢኮኖሚ አተያይን ወደ ብዝኅ ዘርፍ በማሸጋገር እመርታዊ ዕድገት እንዲመዘገብ እያስቻለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ነጠላ የኢኮኖሚ አተያይን ወደ ብዝኅ ዘርፍ በማሸጋገር እመርታዊ ዕድገት እንዲመዘገብ እያስቻለ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 7/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ነጠላ የኢኮኖሚ አተያይን ወደ ብዝኅ ዘርፍ በማሸጋገር እመርታዊ ዕድገት እንዲመዘገብ እያስቻለ መሆኑ ተገለጸ።
በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ትብብር "ኢትዮጵያ - አዲሲቷ የኢንቨስትመንት መዳረሻ" በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትን እያሳደገ ነው
በውይይቱ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በረከት ፍስሃ-ፅዮን፤ ሀገራዊ ለውጡ የኢትዮጵያን ውስን የኢኮኖሚ አተያይ ወደ ብዝኅ ዘርፍ የልማት አቅጣጫ ማሸጋገር አስችሏል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም የነጠላ ዘርፍ ኢኮኖሚን በብዝኅ አተያይ በመቀየር አስተማማኝ የዕድገት ምኅዳር እንዲፈጠር ማድረጉን ገልጸዋል።
ይህም የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮችና የልማት አቅሞች በብዛትና በጥራት የሚስፋፉበትን ምቹ የዕድገት መደላድል መፍጠር እንዳስቻለ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የኢንቨስትመንት ፍሰትና ተወዳዳሪነትን እያሳደገ ነው ብለዋል።
የኢንቨስትመንት ዘርፍ ስኬቶች ተገማችና ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ምኅዳር በመፍጠር በተኪ ምርትና በሥራ ዕድል ፈጠራ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያሻሻለ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍጹም ከተማ በበኩላቸው፤ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እመርታዊ የፖሊሲና የአሰራር ምኅዳር እንዲፈጠር አድርጓል ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮችም የምርታማነት አቅምን በማሳደግ በሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚኖራቸውን ድርሻ በማጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያን ምቹ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የስበት ማዕከል እያደረጋት ይገኛል ያሉት ደግሞ የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሞቱማ ተመስገን ናቸው፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮችም ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የሚሸጋገሩበትን አስቻይ ምኅዳር በመፍጠር ጥራትና ብቃት ያላቸው አልሚዎች መዋለ ነዋያቸውን ፈሰስ የሚያደርጉበትን ዕድል እንደፈጠረ ገልጸዋል፡፡
የሞሐን ግሩፕ ኩባንያዎች ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሀርሽ ኮታሪ፤ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የአልሚ ባለሃብቶችን ትርፋማነት በማሻሻል ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢ መፍጠሩን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፤ በሀገራዊ ለውጡ ማግስት የመገናኛ ብዙኅን የኢትዮጵያን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ የሚገልጡበትን ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
በዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ሥራ የጀመረው የፐልስ ኦፍ አፍሪካን (POA) ጨምሮ የህዝብና የንግድ መገናኛ ብዙኅን የሀገርን የዕድገት ዕድሎች እያስተዋወቁ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በቀጣይም መገናኛ ብዙኅን በተለያዩ የቋንቋ አማራጮች ኢንቨስትመንትን ለማነቃቃት የሚያበረክቱትን ጉልህ አስተዋጽኦ ለማስቀጠል የመረጃ ሰጪ ተቋማት ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።
የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ ለቴክኖሎጂ ትልቅ ትኩረት የሰጠ እና የኢትዮጵያን የእድገት ግስጋሴ የሚያፋጥን አቀጣጣይ ሞተር መሆኑን ተናግረዋል።