ቀጥታ፡

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትን እያሳደገ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 7/2018 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትን እያሳደገ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ገለጹ።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በመተባበር" ኢትዮጵያ - አዲሲቷ የኢንቨስትመንት መዳረሻ" በሚል መሪ ሐሳብ የምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
 
በመድረኩ ላይ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዮሐንስ መስፍን፣ እንዲሁም የፌደራልና የክልል የኢንቨስትመንት ልማት ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
 
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ ባቀረቡት መነሻ ጽሑፍ መንግሥት የጀመረው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ሰፊ አማራጭ ተመልክተው በስፋት እንዲሰማሩ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
 
ማሻሻያው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንዲሳብባቸው ተለይተው በተቀመጡ አምስት ቁልፍ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ትልቅ መነቃቃትን መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ 
 
በዚህም አዳዲስ ባለሀብቶች መግባታቸው ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ ፋይዳ እያበረከተ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡ 
 
ሪፎርሙ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን ጠቁመው የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት በቴክኖሎጂ በማልማት ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ 



 
ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ጠቅሰዋል፡፡ 
 
በቱሪዝም፣ አይ ሲቲ እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፎች መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ዘመናዊና ዲጂታል ኢኮኖሚን በመገንባት ኢንቨስትመንት የመሳብ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
 
ከዚህ ቀደም ዝግ የነበረው የቤት ልማት ዘርፍ በሕግ ማሻሻያ አማካኝነት ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት መሆኑንም አስታውቀዋል።
 
ኮሚሽኑ ባከናወነው የተቀናጀ የማስተዋወቅ ሥራ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ ከ2013 ዓ.ም እስከ 2017 ዓ.ም ዓመታት ውስጥ 18 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ 
 
ነፃ ንግድ ቀጣናዎች ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ የሥነ-ምኅዳር ዕድል መፍጠራቸውን ጠቁመው፤ በቀጣይም ሀገሪቱ በአህጉሪቱ ያላትን የኢንቨስትመንት ደረጃ ይበልጥ ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም