ቀጥታ፡

በጠቅላላ ምርጫው በንቃት በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው የበኩላችንን አስተዋፅኦ እናበረክታለን

ወላይታ ሶዶ፤ መጋቢት 7/2018 (ኢዜአ):- በጠቅላላ ምርጫው በንቃት በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው የበኩላችንን አስተዋፅኦ እናበረክታለን ሲሉ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሴት መምህራን ገለጹ።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለማካሄድ የጊዜ ሰሌዳ  አውጥቶ የመራጮች ምዝገባና ሌሎች የቅድመ ምርጫ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡

መጪው ምርጫን አስመልክተው ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሴት መምህራን እንዳሉት፤ በመጪው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው የበኩላችንን አስተዋፅኦ ለማበርከት ተዘጋጅተናል።

በዩኒቨርስቲው የሒሳብ መዝገብ አያያዝ እና የፋይናንስ ትምህርት ክፍል መምህርት ትዕግስት ደቻሳ፤ ምርጫ ሴቶች ዴሞክራሴያዊ መብታቸውን የሚጠቀሙበት  በመሆኑ ተሳትፏቸውን ማጠናከር ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ሴቶች በሀገሪቱ በምርጫ እኩል ተሳትፎ የሚያደርጉበት ስነ- ምሕዳር የተፈጠረ በመሆኑ እድሉን በመጠቀም የሚፈልጉትን ፓርቲ ወደ ስልጣን ማምጣት ይገባቸዋል ነው ያሉት።

በምርጫው የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ ተመዝግበው ካርድ መውሰዳቸውን ጠቅሰው በሀገሪቱ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና ስኬት የበኩላቸውን ለመወጣት ማቀዳቸውን አስረድተዋል።

ዕድሜያቸው ለምርጫ የደረሰ ሁሉም ሴቶች በድምፃቸው መሪዎቻቸውን የመወሰን ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ያሉት ደግሞ የዩኒቨርስቲው የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት መምህርት ኃይማኖት አዱኛ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ የምርጫ ክርክሮች ፓርቲዎች እንደ ሀገር ይዘው የመጡትን አማራጭ ለማወቅ እድል የፈጠረ በመሆኑ ድምፃቸውን ይበጀኛል ለሚሉት ፓርቲ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።

ሴቶች ተሳትፏቸውን በማጠናከር ለሀገር ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሳለጥ የበኩላቸውን እንዲወጡ የሚጠበቅብንን እንወጣለን ነው ያሉት።

በዩኒቨርቲው የወላይትኛ ትምህርት ክፍል መምህርት አሪፏ ኮራ በበኩላቸው፤ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሴቶች ተሳትፎ የላቀ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ሴቶች በቁጥራቸው ልክ በሁሉም ዘርፎች ከተሳተፉ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል አመልክተው በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ላይ በንቃት ለመሳተፍ የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን ጠቁመዋል።

በድምጽ መስጫ ወቅትም ለሰላምና ልማት ይበጃል ያሉትን ፓርቲ ወደ ስልጣን ለማምጣት መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም