ቀጥታ፡

ቤተ እምነቶች ለዘላቂ ሰላም እና ልማት መረጋገጥ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ማጠናከር አለባቸው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 7/2018 (ኢዜአ)፡-ቤተ እምነቶች ለዘላቂ ሰላም እና ልማት መረጋገጥ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ማጠናከር እንዳለባቸው የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የሃይማኖት ተቋማት ለሕዝቦች ትስስር መጎልበት፣ ለልማትና ሰላም ያላቸውን አዎንታዊ ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “የሃይማኖት ተቋማት በመደመር መንግሥት ዕይታ” በሚል መሪ ሀሳብ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የሃይማኖት አባቶች እና ምዕመናን ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።


 

በመድረኩ የመደመር መንግሥት ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ያለው ምልከታ ላይ ያተኮረ የውይይት ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። 

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በሀገረ መንግስት ግንባታ ውስጥ የማይተካ ሚና መጫወቷን ገልጸዋል።

እንዲሁም ትውልድን በመቅረጽ፣ቅርስ እና ታሪኮችን ጠብቃ ማቆየቷን ተናግረዋል።

የመደመር መንግሥት ለዚህ እውቅና እንደሚሰጥ ገልጸው፤ እነዚህ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

የቤተ እምነቶች ትልቁ ሀላፊነት የሰላም አምባሳደርነት መሆኑን ገልጸው፤ ለዘላቂ ሰላም እና ልማት መረጋገጥ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ማጠናከር እንዳለባቸው አመላክተዋል።


 

እምነትን ሽፋን ያደረጉ ህገወጥ ድርጊቶችን በጋራ መከላከል እንደሚገባ ጠቁመው፤ የማምለኪያ ስፍራዎችን በተመለከተም ችግሮችን በመፈተሽ በፍትሀዊነት ተገቢው ምላሽ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ በበኩላቸው፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ተጨባጭ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ለመፍታት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም