የሃይማኖት ተቋማት ለሕዝቦች ትስስር መጎልበት፣ ለልማትና ሰላም ያላቸውን አዎንታዊ ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖት ተቋማት ለሕዝቦች ትስስር መጎልበት፣ ለልማትና ሰላም ያላቸውን አዎንታዊ ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2018 (ኢዜአ)፡- የሃይማኖት ተቋማት ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ፣ ለሕዝቦች ትስስር መጎልበት፣ ለልማትና ሰላም ያላቸውን አዎንታዊ ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የሃይማኖት ተቋማት የሰላም ግንባታና የልማት ስራዎች ላይ ያላቸውን አስተዋፅኦ ሊያጠናክሩ ይገባል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “የሃይማኖት ተቋማት በመደመር መንግስት ዕይታ” በሚል መሪ ሀሳብ በከተማዋ ከሚገኙ የእስልምና እምነት አባቶች እና ምዕመናን ጋር የማጠቃለያ መድረክ አካሂዷል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች መንግስት የህዝበ ሙስሊሙን ጥያቄ እየፈታ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት ለትውልዱ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ላይ እያከናወነ ያለውን ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።
ለሀገር ሰላም እና ዕድገት በጋራ በመቆም የሚጠበቅባቸውን ሚና እንደሚወጡም ገልጸው፤ ለዘላቂ ሰላም ያላቸውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
በተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ላይ ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ ጀማሉ ጀንበር (ዶ/ር)፤ ከተማ አስተዳደሩ ከህዝበ ሙስሊሙ ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
እስካሁንም በርካታ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘታቸውን እና በቀጣይም በሂደት ምላሽ እየተሰጠ እንደሚሄድ ተናግረው ህዝበ ሙስሊሙ ነባራዊ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መንገድ መንቀሳቀስ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድር በበኩላቸው፤ የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች በየደረጃው ምላሽ እያገኙ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም የሚነሱ ጥያቄዎች በየደረጃው እየተፈቱ እንደሚሄዱ ጠቅሰዋል፡፡
የተገኙ ስኬቶችን ማስጠበቅ እንደሚገባ አመልክተው ህዝበ ሙስሊሙ በጋራ በመንቀሳቀስ ለልማት እና እድገት ሚናውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ህዝበ ሙስሊሙ ለሀገረ መንግስት ግንባታ ወሳኝ ሚና እንደነበረው እና አሁንም ይህንን እያደረገ ነው ብለዋል።
ቅርስ እና ታሪኮችን እንዲሁም ትውፊት እና እሴቶችን በማቆየት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረው አሁንም አዳዲስ እሴቶችን በመጨመር ማጉላት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
መንግስት ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች በየደረጃው ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ህዝበ ሙስሊሙ ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቅሰው ለባዳ እና ባንዳ እድል ባለመስጠት ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ መቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከሌሎች እምነቶች ጋርም በልማት እና በተለያዩ ስራዎች ላይ በጋራ መስራት እንዳለባቸው ገልጸው፤ ትብብርን ይበልጥ ማጎልበት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ህዝበ ሙስሊሙ ውስጣዊ አንድነቱን ማጠናከር እንዳለበት እና ከተማ አስተዳደሩ ለሚነሱ ጥያቄዎች በቅደም ተከተልና በፍትሃዊነት ምላሽ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል፡፡