ቀጥታ፡

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም በተለያዩ ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል-  ምሁራን

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 7/2018(ኢዜአ)፡-ለውጡን ተከትሎ መንግሥት ተግባራዊ ያደረገው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም የምርት መጠንን በማሳደግና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን የተለያዩ የኢኮኖሚ ምሁራን  ገለጹ።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትን እያሳደገ ነው

መንግሥት የተከተለው የብዝሃ-ዘርፍ ኢኮኖሚ ስትራቴጂም ኢኮኖሚው በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ ጥገኛ እንዳይሆን በማድረግ ለዘላቂ ሀገራዊ ዕድገት አስተማማኝ መሠረት መጣሉንም ገልጸዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢኮኖሚ ምሁራን እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም እና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ነባር መዋቅራዊ ተግዳሮቶችን በመፍታትና የገበያ መረጋጋትን በማምጣት ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ጀማል መሀመድ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ከለውጡ በፊት በነበረው የኢኮኖሚ መዋቅር የውጭ ኩባንያዎች በሀገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ ላይ ያላቸው ተሳትፎ የተገደበ ነበር። 


 

ይህም ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ሰፊ የገበያ ዕድሎችን እንዳያገኙና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲቀዘቅዝ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልፀዋል።

በመሆኑም ሀገሪቱ በውጭ ምንዛሬ እጥረትና በከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ እንድትቆይ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

ለውጡን ተከትሎ ቀደም ሲል የነበሩት የፖሊሲ ማነቆዎች ተወግደው በምትኩ ምቹ ምህዳር መፈጠሩ የኢኮኖሚውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግና የግል ዘርፉን ለማነቃቃት ወሳኝ ሚና መጫወቱን  ተናግረዋል።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም እንደ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ የባንክ አገልግሎት፣ የችርቻሮ ንግድ እና የኮንስትራክሽን ዘርፎችን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት በማድረግ አዲስ የገበያ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።  

የዚህ ሪፎርም ትግበራ እንደ ሳፋሪኮም ያሉ ግዙፍ የዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ኢንቨስት እንዲያደርጉ አስችሏል ብለዋል።

በእነዚህ ስትራቴጂካዊ ዘርፎች ውስጥ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በንቃት መሳተፍ መቻላቸው የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና በሀገር ውስጥ ያለውን የአገልግሎት ጥራትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ከፍተኛ ፋይዳ ማስገኘቱን ጠቁመዋል።

በሪፎርሙ የውጭ ምንዛሬ በገበያ እንዲወሰን መደረጉ፣ የመንግሥት ገቢና ወጪን የማመጣጠን ስራ እና የታክስ መሰረቱን ማስፋት ለኢኮኖሚው ስኬት ትልቅ መገለጫዎች መሆናቸውን አንስተዋል።

በተለይም ለማዕድን ዘርፍ በተሰጠው ልዩ ትኩረት በወርቅ ምርትና ግብይት ላይ የተመዘገቡ ውጤቶች የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ግኝት በማሳደግ ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል ብለዋል።


 

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር ከፍተኛ ተመራማሪ ሞላ አለማየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በሪፎርሙ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታቱ ፖሊሲዎች መተግበራቸውን ገልጸዋል።

ይህም የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ እያሳደገው መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፉን ዲጂታላይዝ  ማድረግ መቻሉ፣ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት እያሳደገው መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም