ቀጥታ፡

የፊቼ ጫምባላላ በዓል እሴት ለአብሮነትና ህብረ ብሔራዊ አንድነት መሰረት ነው

ሀዋሳ ፤መጋቢት 6/2018 (ኢዜአ)፡-በይቅርታና ምህረት ዘመን የሚቀየርበት የፊቼ ጫምባላላ በዓል እሴት ለአብሮነትና ህብረ ብሔራዊ አንድነት መሰረት ነው ሲሉ የሲዳማ የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።

ፊቼ ጫምባላላ በዓል የህዝቦችን ትስስርና አንድነት በማጠናከር ኢትዮጵያዊነት የሚጎላበት ነው-የበዓሉ ተሳታፊዎች

የሲዳማ ዘመን መለወጫ የፊቼ ጫምባላላ በዓል በሀዋሳ ሶሬሳ ጉዱማሌ በተለያዩ ክዋኔዎች ታጅቦ ተከብሯል።

በበዓሉ አከባበር ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የሀገር ሽማግሌዎች እንዳሉት፤ በይቅርታና ምህረት አዲሱን ዘመን በአዲስ ተስፋ መቀበያ የሆነው የፊቼ ጫምባላላ በዓል እሴቶች ለአብሮነትና ህብረ ብሔራዊ አንድነት መሰረት ነው።

የሲዳማ የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ሻምበል በላይ ሲዳማ በዘመናት መካከል ያዳበረው የፊቼ ጫምባላላ በዓል በውስጡ በርካታ ዕሴቶች እንዳሉት አንስተው በተለይም ሰላም፣ አንድነት፣ አብሮነትና ፍቅርን የያዘ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ፊቼ ጫምባላላ ሰው የሆነ ሁሉ ያለምንም ልዩነት በጋራ የሚበላበት፣ የሚጠያየቅበትና የሚደሰትበት መሆኑን አንስተው ይህም ለህብረ ብሔራዊ አንድነታችን መሰረት ነው ብለዋል።

በዓሉ ዘመን መሻገሪያ እንደመሆኑ ቂምና ቁርሾን በማስወገድ ዘላቂ ሰላምን በመትከል የሚሻገሩበት መሆኑን ጠቅሰው ይህም በዜጎች መካከል ለሚኖረው ጠንካራ አብሮነትና  ትስስር መሰረትና ጉልህ ሚና ያለው ድንቅ ባህል መሆኑን ገልጸዋል።

የሲዳማ ዘመን መለወጫ የፊቼ ጫምባላላ በዓል ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ማህበረሰብ ድረስ በዕርቅና በሰላም በአንድ መንፈስ አዲሱን ዘመን የሚቀበሉበት ባህል መሆኑን ያነሱት ሌላኛው የሀገር ሽማግሌ አቶ ኑሬ ኑካ ናቸው።


 

በፊቼ ጫምባላላ የሲዳማ አባቶች ይመካከራሉ፣ ትናንትን ይገመግማሉ፣ ውጤታማ የሆኑትን ያበረታታሉ፣ ስኬት ያጡትን አቅጣጫ ያሳያሉ፣ የሀገር ደህንነት መጠበቅ ላይ ይወያያሉ ብለዋል።

ሌላኛው የሀገር ሽማግሌ አቶ መኩሪያ መልከኛ በበኩላቸው ፊቼ ጫምባላላ በአሮጌው ዓመት የተሰሩ በደሎችን በይቅርታ ሽረን ወደ አዲሱ ዘመን የምንሸጋገርበት በውስጡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕሳቤዎችን የያዘ በዓል መሆኑን ነው የገለፁት።


 

ልዩነትንና መከፋፈልን ፈጽሞ የማይደግፈው ዕሴቱ ለሀገር ሰላምና ለህዝቦች አንድነት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ባህሎቻችን የአንድነታችንና የትስስራችን መሰረት ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም