ፊቼ ጫምባላላ በዓል የህዝቦችን ትስስርና አንድነት በማጠናከር ኢትዮጵያዊነት የሚጎላበት ነው-የበዓሉ ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
ፊቼ ጫምባላላ በዓል የህዝቦችን ትስስርና አንድነት በማጠናከር ኢትዮጵያዊነት የሚጎላበት ነው-የበዓሉ ተሳታፊዎች
ሀዋሳ ፤መጋቢት 6/2018 (ኢዜአ)፡- ) ፊቼ ጫምባላላ የህዝቦችን ትስስርና አንድነት በማጠናከር ኢትዮጵያዊነት የሚጎላበት በዓል መሆኑን በበአሉ የታደሙ የህብረተሰብ ተወካዮች ገለጹ።
ፊቼ ጫምባላላ አንድነትና አብሮነትን በመስበክ ለማህበራዊ ትስስር መጠናከር ጉልህ ሚና አለው
የሲዳማ ዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በሶሬሳ ጉዱማሌ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
በዓሉን ለመታደም ከተለያዩ አካባቢዎች የተገኙት የህብረተሰብ ተወካዮች በዓሉ የህዝቦችን ትስስርና አንድነትን በማጠናከር ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
የሀዲያ የባህል ሽማግሌ የሆኑት ሁንድገራድ ገብረዮሃንስ ኤርዲሎ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ፊቼ ጫምባላላ የሲዳማ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊያን በዓል ነው።
የሀዲያና ሲዳማ ህዝቦች የጋራ እሴት ያላቸውና በታሪክና በባህል የተሳሰሩ መሆናቸውን ገልጸው የአደባባይ በዓላትን በጋራ ማክበር የህዝቦችን ትስስርና አንድነት የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ የሚወጣበት እድል እንደሚፈጠር ጠቅሰው በበዓሉ በመታደማቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከከምባታ ዞን የመጡት ወይዘሮ አስካለ ሳፎ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያዊያን በጋራ የሚያከብሩት በዓል ለህዝቦች ትስስርና አብሮነት መጠናከር ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
ፊቼ ጫምባላላ የባህል ትውውቅ ለማድረግ፣ በህዝቦች ዘንድ መቻቻልና አንድነት እንዲኖር እድል የሚፈጥርና በሀገር ግንባታ ሂደት ህዝቦች የጋራ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡
በዓሉን ለመታደም በዋዜማው ሀዋሳ መግባታቸውን የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዋ በቆይታቸው የህዝቡን የእንግዳ ተቀባይነት ባህል በማየታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
እንደ ፊቼ ጫምባላላ ያሉ የአደባባይ በዓላት የህዝቦችን ትስስርና ህብረብሄራዊ አንድነትን እንደሚያጠናክሩ የገለጹት ደግሞ ከሃላባ ዞን የመጡት አቶ አሩና አህመድ ናቸው፡፡
በበአሉ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች መታደማቸውን ገልጸው ህዝቦች በጋራ የሚያከብሯቸው በዓላት ሰላምን ለመፍጠር፣ አብሮነትና አንድነትን ለማጠናከር ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ዛሬ በሶሬሳ ጉዱማሌ በተከበረው የፊቼ ጫምበላላ በዓል ከተለያዩ ክልሎችና ዞኖች የተጋበዙ ልኡካን የተሳተፉ ሲሆን ለበዓሉ ያላቸውን ክብር ለመግለጽም የተለያዩ ስጦታዎችን አበርክተዋል፡፡