በመተባበር ይህን አስቸጋሪ ጊዜ እናልፈዋለን - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በመተባበር ይህን አስቸጋሪ ጊዜ እናልፈዋለን - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
አርባምንጭ ፤ መጋቢት 6 /2018 (ኢዜአ)፦ አንድ ሆነን በመተባበር ይህን አስቸጋሪ ጊዜ እናልፈዋለን ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ተናገሩ፡፡
ኢትዮጵያውያን ወገኖች እያደረጉልን ባለው ሰብአዊ ድጋፍ ተጽናንተናል
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በጋጮ ባባ ወረዳ ላካ ቀበሌ በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን የማጽናናት ስነ ስርአት ተካሄዷል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ጥላሁን በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በመተባበርና ዘርፈ ብዙ ድጋፍ በማድረግ የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም የክልሉ መንግስት እየሠራ ይገኛል።
አንድ ሆነን በመተባበር ይህን አስቸጋሪ ጊዜ እናልፈዋለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ድጋፉ ወደ ስፍራው በአግባቡ እንዲደርስ የመንገድ መሠረተ ልማት ጥገናም ጎን ለጎን እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
ሰብአዊ ድጋፍ እያደረጉ ላሉ አካላት ምስጋና ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የተጎዱ ወገኖችን ሰብአዊና ማህበራዊ አገልግሎቶችን በማጠናከርና በማጽናናት የስነ-ልቦና ግንባታ መስጠት እንደሚገባም ገልጸዋል።
የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት መላው ኢትዮጵያውያንና ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ወገኖች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ(ዶ/ር)፤ በዞኑ በአራት ወረዳዎች የተከሰተው የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደን ጨምሮ ከፍተኛ የፌደራልና የክልል አመራሮች በአደጋው ቦታ ተገኝተው በመጠየቃቸው ህዝቡ አየተጽናና ይገኛልም ብለዋል።
ተፈናቃይ ወገኖችን በጊዜያዊም ሆነ በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም የዞኑ አስተዳደር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የመንግስት አካላትና መላው ኢትዮጵያዊያን እያደረጉ ባሉት ድጋፍ እና ማጽናናት ዋና አስተዳዳሪው ምስጋና አቅርበዋል።