ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን ወገኖች እያደረጉልን ባለው ሰብአዊ ድጋፍ ተጽናንተናል

አርባምንጭ ፤ መጋቢት 6 /2018 (ኢዜአ)፦በሁሉም አቅጣጫ ኢትዮጵያውያን ወገኖች በመረባረብ እያደረጉልን ባለው ሰብአዊ ድጋፍ ተጽናንተናል ሲሉ በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ የተፈናቀሉ ወገኖች ገለጹ።

በመሬት መንሸራተት አደጋው ለተጎዱ ወገኖች የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል -የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

በዞኑ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ተፈናቅለው በጊዜያዊ ስፍራ ተጠልለው ለሚገኙ ወገኖች የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ባለሀብቶች ሰብአዊ ድጋፍ እያደረጉላቸው ይገኛል።


 

ከተፈናቃዮች መካከል በጋጮ ባባ ወረዳ የማዞ ዶይሳ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ዳመነ ደበበ፤በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ልጄ እና ባለቤቴን ጨምሮ አራት ቤተሰብ አባላትን አጥቻለሁ ብለዋል።

የደረሰብን አደጋ ቤተሰቦቻችንና ንብረታችን አሳጥቶን ከቀያችን እንድንፈናቀል አድርጎናል ብለዋል።


 

አደጋው እጅግ ከባድ ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደን ጨምሮ ኢትዮጵያውያን እስከ ስፍራው በመምጣት እየጠየቁን በመሆኑ እየተጽናናን ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የተለያዩ አካላት በመረባረብ አስፈላጊውን ሰብአዊ ድጋፍ እያደረጉላቸው በመሆኑ መጽናናታቸውን ጠቅሰው ጉዳቱ ከፍተኛ በመሆኑ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ሌላው በጋጮ ባባ ወረዳ ላካ ቀበሌ ተፈናቃይ አቶ ናጄ ዳዳ በአደጋው ልጄን እና ሙሉ ንብረቴን አጥቻለሁ ብለዋል።


 

የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ኢትዮጵያውያን ወገኖች እስከ ቦታው መጥተው በመጠየቃቸው ተጽናንተናል ሲሉም ተናግረዋል።

የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ባለሀብቶች ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ድጋፍ እያደረጉልን ይገኛሉ ብለዋል።

የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቅሰው በዘላቂነት ለማቋቋም መንግስትና መላው ኢትዮጵያዊያን ከጎናቸው እንዲቆሙ ጠይቀዋል።


 

ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ ከጤና አገልግሎት ጀምሮ የተለያየ ሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገልን ይገኛል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ካረሶ ካልሌ ናቸው።

የደረሰብን አደጋ ከባድ ቢሆንም በሁሉም አቅጣጫ ኢትዮጵያዊያን በመረባረባቸው ተጽናንቻለሁ ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት በጋጮ ባባ ወረዳ ላካ ቀበሌ በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን የማጽናናት ስነ ስርአት እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም