ቀጥታ፡

የሃይማኖት ተቋማት የሰላም ግንባታና የልማት ስራዎች ላይ ያላቸውን አስተዋፅኦ ሊያጠናክሩ ይገባል 

ሐረር፤መጋቢት 6/2018 (ኢዜአ)፡- የሃይማኖት ተቋማት የሰላም ግንባታና የልማት ስራዎች ላይ ያላቸውን አስተዋፅኦ ሊያጠናክሩ ይገባል ሲሉ የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ዑመር ገለጹ። 

በሐረር ከተማ አሚር አብዱላሂ አዳራሽ "በመደመር መንግሥት እይታ የኃይማኖት ተቋማት ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ ከእስልምና እምነት አባቶች ጋር የተዘጋጀ ክልል አቀፍ የምክክር መድረክ ዛሬ ተካሂዷል። 


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ዑመር እንደገለጹት፣ መንግስት ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥና የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል።

በተግባራዊ ስራዎችም ኢኮኖሚያዊ እድገት እየተመዘገበና የህዝብ የልማት ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ሰላምና ልማትን ለማስቀጠል በሚሰሩ ሥራዎችም የሃይማኖት ተቋማት ከፍተኛ ሚና እያበረከቱ መሆኑን እንዲሁ፡፡ 

በተለይም ተቋማቱ ህዝቡን በማስተባበር ለሰላም፣ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት መረጋገጥ የላቀ ድርሻቸውን ሲወጡ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል። 

መንግሥትም ለሃይማኖት ተቋማት መጠናከርና መጎልበት በርካታ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አውስተዋል። 

ተቋማቱ ለሀገር ህልውናና ሉዓላዊነት መከበር አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠቅሰው፤ አሁንም ትውልዱን በሥነ-ምግባር በማነፅ ሀገሩንና ህዝቡን እንዲያገለግል  የጎላ ሚና እየተጫወቱ ነው ብለዋል። 

ሰላምን በማጽናት ልማት እንዲፋጠን የሚጠበቅባቸውን ማህበራዊ ኃላፊነት አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አመልክተዋል። 


 

የመድረኩ ተሳታፊዎችም በክልሉ በተከናወኑ የሰላምና ልማት ስራዎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተው፤ ለወደፊቱም ከመንግስት ጎን ሆነው የተጀመሩትን የተቀናጀ የሰላምና የልማት ተግባራት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም