ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው በምርምር የወጡ ምርታማ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ ነው

ጎንደር ፤መጋቢት 6/2018 (ኢዜአ)፡- የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለአካባቢው ስነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑና ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የተሻሻሉ የሰብልና የፍራፍሬ ዝርያዎችን በማላመድ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡

በአማራ ክልል ምርታማነትን የሚያሳድጉ የምርምር ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

በዩኒቨርሲቲው የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዳንኤል ንጉሴ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በኮሌጁ ሥር በተቋቋሙት አራት የምርምር ጣቢያዎች የግብርና ምርምር ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡

በዚህም በሽታን፣ ተባይንና የዝናብ እጥረትን በመቋቋም ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችሉ የሩዝ፣ የሽንብራና የቢራ ገብስ ዝያዎችን በምርምር በማውጣት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በምርምር የወጡት የሰብል ዝርያዎችም የአካባቢውን ስነ ምህዳር መሰረት ያደረጉና ምርታማነታቸው የተረጋገጠ በመሆኑ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በምዕራብ በለሳ፣ በጎንደር ዙሪያ፣ በምዕራብና ምስራቅ ደንቢያ ወረዳዎች በሩዝ ሰብል ከ30 ኩንታል በላይ፣ በሽንብራ ደግሞ እስከ 25 ኩንታል ምርት በሄክታር የሚሰጡ ናቸው ብለዋል።

ይህም እስካሁን ከነበረው የአካባቢው የሰብል ዝርያ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ የምርት ጭማሬ የሚያስገኙ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በፍራፍሬ ልማት ዘርፍም በጎርጎራ አካባቢ ባቋቋመው የምርምር ጣቢያ በመታገዝ የሙዝ፣ የአቮካዶ፣ የማንጎና የፓፓያ ዝርያዎችን በስፋት የማላመድ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡


 

ኮሌጁ በአዳዲስ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሃሳቦች ላይ የተመሰረቱ የምርምር ስራዎችን በማከናወን የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ 

በተጨማሪም አዲስ ስርአተ ትምህርት በመቅረጽ በዲግሪ መርሃ ግብር የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን እያሰለጠነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው ሥር የግብርና ኮሌጁ ባቀረበልኝ የተሻሻለ የሽንብራ ዘር ተጠቅሜ በማልማት ከራስ ፍጆታ ያለፈ ምርት በማምረት ተጠቃሚ መሆን ችያለሁ ያሉት የምእራብ በለሳ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ታምራት በየነ ናቸው፡፡ 

የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ጣሰው በላይ በበኩላቸው፤ ኮሌጁ ያቀረበላቸውን የሩዝ ዝርያ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ በመዝራት 20 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

የሩዝ ዝርያው ለአካባቢው ስነ ምህዳር ተስማሚ ከመሆኑም በላይ በሽታንና የዝናብ እጥረትን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጥ መሆኑን በተግባር ሞክሬ አረጋግጫለሁ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም