ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ምርታማነትን የሚያሳድጉ የምርምር ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ባህርዳር፤ የካቲት 30/2018(ኢዜአ)፦ በክልሉ የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት የሚያሳድጉ የምርምር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ።

የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዓመታዊ ክልላዊ የግብርና ምርምር ስራዎች አውደ ጥናት በባህር ዳር ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።


 

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ደረጀ ማንደፍሮ በወቅቱ እንደገለጹት የ25 ዓመት የአሻጋሪ ዕድገትና ዘላቂ ልማት ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር ተገብቷል።

በመሆኑም በክልሉ የሚገኙ እምቅ አቅሞችን ለማልማት በሚደረገው ጥረት ተመራማሪዎች፣ ምሁራንና ተባባሪ አካላት በተቀናጀ መልኩ መስራት ይኖርብናል ብለዋል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የምርምር ስራዎች አማካይ የሰብል ምርትማነት በሄክታር ከ10 ኩንታል ወደ 32 ኩንታል ማደጉን ጠቅሰው በተለይም የስንዴ ምርታማነት ከፍተኛ ማንሰራራት እያሳየ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት የሚያሳድጉና ችግሮችን የሚፈቱ የምርምር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

በምርምር አበረታች  ውጤቶች ቢመዘገብም የአፈር አሲዳማነት፣ የግብርና መካናይዜሽን ዕጥረት፣ የድህረ ምርት ብክነትና ሌሎች ችግሮች እየተፈቱ መሄድ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። 


 

የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰማኽኝ አስረዴ(ዶ/ር)፤ ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ዓመታት የአርሶ አደሩን ኑሮ ሊቀይሩ የሚችሉ ዘርፈ ብዙ የምርምር ስራዎች ማከናወኑን ገልጸዋል።

በዚህም በሰብልና እንስሳት ልማት፤ በአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ በደን ልማት ስኬታማ ውጤቶች መገኘታቸውን አንስተው በምግብ ሳይንስና በባዮ ቴክኖሎጂ የተገኙ ውጤቶችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ ግብርናውን ለማዘመን አሁን ላይ 960 የተለያዩ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አንስተው 371 የሚሆኑትን ዘንድሮ ለማጠናቀቅ መታቀዱን ተናግረዋል። 


 

የአማራ ክልል የዩኒቨሲቲዎች ፎረም ዋና ጸሀፊ ተወካይ ጀጃው ደማሙ(ዶ/ር)፤ በበኩላቸው ከግብርና ምርምርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የአርሶ አደሩን ኑሮ የሚቀይሩና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የምርምር ስራዎች ትኩረት እንደተሰጣቸው አንስተዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም