ቀጥታ፡

በዞኑ እየተከናወኑ የሚገኙ የመንገድ መሰረተ ልማቶች የማህበረሰቡን ችግር በተጨባጭ የሚቀይሩ ናቸው

፤ መጋቢት 6/2018 (ኢዜአ)፦ በኢሉአባቦር ዞን በተያዘው ዓመት እየተከናወኑ የሚገኙ የመንገድ መሰረተ ልማቶች በክረምትም ሆነ በበጋ አገልግሎት የሚሰጡና የማህበረሰቡን ማህበራዊ ችግር በተጨባጭ የሚቀይሩ መሆናቸውን የዞኑ መንገድና ሎጂስቲክስ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

በግብርናው ዘርፍ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ውጤት እየተመዘገበበት ነው

የኢሉአባቦር ዞን መንገድና ሎጂስቲክስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጣሰው አሰፋ እንደገለፁት፤ በዞኑ ወደ 250 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የመስመር ዝርጋታና የነባር መስመሮች ጥገናን ጨምሮ የ4 አዳዲስ ድልድዮች ግንባታ እየተከናወነ ነው።

የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታው ወረዳን ከወረዳ እንዲሁም በወረዳ ውስጥ ለውስጥ ቀበሌን ከቀበሌ የሚያገናኙ የአዳዲስ መስመሮች ዝርጋታና ነባር መስመሮች ጥገናና ደረጃ ማሳደግን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በተለይ በወረዳዎች ውስጥ ለውስጥ ቀበሌን ከቀበሌ የሚያገናኙ 16 የመንገድ ግንባታን ጨምሮ ከ32 ኪሎ ሜትር በላይ የአዳዲስ መንገዶች ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል።

እንዲሁም የነባር መንገዶች የጥገናና ደረጃ ማሻሻል ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው የ4 አዳዲስ ድልድዮች ግንባታም እየተከናወነ ስለመሆኑም አክለዋል።

ከለውጡ ወዲህ በዞኑ በተለይ ለገጠር መንገዶች ተደራሽነት በተሰጠው ትኩረት ወረዳን ከወረዳና ቀበሌንም ከቀበሌ የሚያገናኙ የ45 መንገዶች ግንባታ ተከናውኗል ብለዋል።

በዞኑ በተያዘው ዓመት እየተከናወኑ የሚገኙ የመንገድ መሰረተ ልማቶች በክረምትም ሆነ በበጋ አገልግሎት የሚሰጡና የማህበረሰቡን ማህበራዊ ችግር በተጨባጭ የሚቀይሩ መሆናቸውንም ኃላፊው አመልክተዋል።

በዞኑ የአሌ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ያደታ ዲሳሳና አቶ ግርማ አባተ፤ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመንገድ ዝርጋታና ደረጃ ማሳደግ የተሰሩ ስራዎች ከአጎራባች ወረዳ ቀበሌዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዲጠናከር ማድረጉን ገልጸዋል።


 

መንገዶቹ በክረምትም ሆነ በበጋ አገልግሎት ስለሚሰጡ የማህበራዊ ግንኙነት መጠናከር ብቻም ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዳሳደገላቸው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ አክለውም በተለይ በኦኖኑ ቀበሌ በጉመሮ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ የዘመናት የሕዝብ ጥያቄን የመለሰ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው በወንዝ ሙላት ምክንያት ይጠፋ የነበረን የሰው ህይወት የታደገ ነው ብለዋል።

በአካባቢያቸው የተገነቡት መንገዶችና ድልድዮች የቀደሙ ችግሮቻቸውን የቀረፉላቸውና ተጠቃሚነታቸው እንዲጨምር እያደረጉ እንደሚገኙ የገለፁት ደግሞ በዞኑ የዲዱ ወረዳ ነዋሪዎቹ አቶ ደሳለኝ ደጋጋ እና ወይዘሮ ደመቀች ረጋሳ ናቸው።

በተለይ በዲቦ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻቸው ላይ የነበረውን ተፅዕኖ እንደቀረፈላቸውም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም