በግብርናው ዘርፍ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ውጤት እየተመዘገበበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
በግብርናው ዘርፍ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ውጤት እየተመዘገበበት ነው
ወላይታ ሶዶ ፤መጋቢት 4/2018(ኢዜአ):- በግብርናው ዘርፍ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑ ተመላከተ።
የፌዴራልና የክልል የመንግስት ስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሴት ምሁራን በወላይታ ዞን ቦዲቲ ከተማ በሴት አባላት የተደራጁ ማህበራትን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።
ጉብኝቱን የታደሙት የኢትዮጵያ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ የሺእመቤት ነጋሽ በወቅቱ እንዳሉት በግብርናው ዘርፍ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ውጤት እየተመዘገበበት ነው ብለዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልልም በዘርፉ በተደራጁ ሴቶች የተጀመረው ስራ ገቢ ከማስገኘት ጎን ለጎን ጤናማ ህብረተሰብን ለመፍጠር፣ የሌማት ትሩፋት ግብን ለማሳካትና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ አጋዥ ድርሻ እየተወጣ ነው ያሉት።
ኮርፖሬሽኑም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የግብርና ግብአቶችን፣ ማሽነሪዎችን እና የፋይናንስ ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በክልሉ ሴቶች የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው በተለያዩ ዘርፎች በመሰማራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወላይቴ ቢቶ ናቸው።
በዚህም በርካታ ሴቶች ተጠቃሚ ሆነው ከጠባቂነት በመላቀቅ የራሳቸውን ሀብት ማፍራት መጀመራቸውን ጠቁመዋል።
የክልሉ ምክር ቤትም ሴቶች በተደራጀ መልኩ በኢንተርፕራይዝ ተሰማርተው ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን አንስተው አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
በማህበር ተደራጅተው በወተት ላም እርባታ ላይ መሰማራታቸውን የገለፀችው ወጣት ኤልሳቤጥ ትዕግስቱ ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት በአምስት የወተት ላሞች የጀመሩት ስራ አሁን ላይ 32 መድረሳቸውን ጠቁማለች።
ማህበራቸው ስምንት ሚሊዮን ብር ካፒታል ማስመዝገቡን ገልጻ ለ18 ሰዎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠራቸውንም አስረድታለች።
በርትተው ከሰሩ በአጭር ጊዜ መለወጥ ይቻላል የምትለው ወጣቷ መንግስት ባመቻቸላቸው የመሸጫ ሱቅ ለከተማው ህብረተሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ ወተት እያቀረቡ መሆናቸውንና ስራውን በሰፊው ለመስራት ማቀዳቸውንም ገልጻለች።
"እቴቴ የእንጀራ መጋገርና ማከፋፈል" ስራ ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ አይናለም ጌታ በበኩላቸው በአካባቢው በቤተሰብ ፓኬጅ ተደራጅተው በ10 ሺህ ብር ካፒታል አምስት ሆነው ወደ ስራ መግባታቸውን አስታውሰዋል።
በ2012 ዓ.ም በመኖሪያ ቤታቸው የጀመሩት ስራ አሁን አድጎ ካፒታላቸው ከ350 ሺህ ብር መብለጡን ጠቁመው ለተጨማሪ 11 ሴቶች ጊዜያዊ እና ቋሚ የስራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውንም ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩም የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው ስራቸውን ለማዘመንና ለማሳደግ ማቀዳቸውንም አመልክተዋል።