ቀጥታ፡

ነገሌ አርሲ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ይጫወታል 

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጠናቀቃል። 

ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ነገሌ አርሲ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከልደታ ክፍለ ከተማ ጋር ይጫወታል

ነገሌ አርሲ በውድድር ዓመቱ 23 ጨዋታዎችን አከናውኖ በ10ሩ ሲያሸንፍ አምስት ጊዜ ተሸንፏል። በስምንት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል።  

22 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 14 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ነገሌ አርሲ በ38 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 23 ጨዋታዎች ስምንቱን ሲያሸንፍ በአምስቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪው 10 ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 17 ግቦችን ሲያስቆጥር 13 ግቦችን አስተናግዷል። 

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ34 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል። 

ነገሌ አርሲ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። ካሸነፈ ሁለተኛ ደረጃን ከሃዋሳ ከተማ ይረከባል። 

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ካሸነፈ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል። 


 

በሌላኛው መርሐ-ግብር መቀሌ 70 እንደርታ ከወላይታ ድቻ  ከቀኑ 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

መቀሌ 70 እንደርታ በውድድር ዓመቱ ባካሄዳቸው 23 ጨዋታዎች አራቱን አሸንፎ በዘጠኙ ተሸንፎ 10 ጊዜ አቻ ተለያይቷል።15 ግቦችን ሲያስቆጥር 25 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ22  ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።  

ተጋጣሚው ወላይታ ድቻ በሊጉ ካደረጋቸው 23 ጨዋታዎች መካከል አምስቱን በድል ሲወጣ ሰባት ጊዜ ተሸንፏል። በ11 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። በ23ቱ ጨዋታዎች ላይ 26 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ በተመሳሳይ 26 ጎሎች ገብተውበታል። 

ወላይታ ድቻ በ26 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

መቀሌ 70 እንደርታ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች አላሸነፈም። ቡድኑ ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ይጫወታል። 

በ23ኛ ሳምንት የሊጉን መሪ ሲዳማ ቡናን 3 ለ 1 ያሸነፈው ወላይታ ድቻ በበኩሉ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይፋለማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም