ቀጥታ፡

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከልደታ ክፍለ ከተማ ጋር ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል።

 

ከቀኑ 7 ሰዓት ልደታ ክፍለ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ በንክ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ልደታ ክፍለ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው 18 ጨዋታዎች መካከል ያሸነፈው አራት ብቻ ነው። በ11ዱ ሲሸነፍ በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 21 ግቦችን ሲያስቆጥር 34 ጎሎችን አስተናግዷል።

ቡድኑ በ15 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ በ18 ጨዋታዎች 15 ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 47 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ሰባት ጎሎች ተቆጥረውበታል።

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ47 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ንግድ ባንክ በሊጉ ከፍተኛ የግብ መጠን ያስቆጠረ እና አነስተኛ ጎል ያስተናገደ ክለብ ነው።

ልደታ ክፍለ ከተማ በ17ኛ ሳምንት በሊጉ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ካስተናገደው የ4 ለ 2 ሽንፈት በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካሸነፈ የሊጉን መሪነት በጊዜያዊነት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ይረከባል።

 

በሌላኛው መርሐ-ግብር ቦሌ ክፍለ ከተማ ከአዳማ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ቦሌ ክፍለ ከተማ በሊጉ 18 ጨዋታዎች አድርጎ ስምንት ጊዜ ድል ሲቀናው በአራቱ ተሸንፏል። በቀሪ ስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 22 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 17 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

ቡድኑ በ30 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።

በውድድር ዓመቱ ካከናወናቸው 18 ጨዋታዎች መካከል አምስቱን ብቻ ያሸነፈው አዳማ ከተማ በስምንቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ አምስት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል።

በ18ቱ ጨዋታዎች 13 ግቦችን ሲያስቆጥር 27 ጎሎችን አስተናግዷል። አዳማ ከተማ በ20 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ቦሌ ክፍለ ከተማ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።  አዳማ ከተማ ካሸነፈ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት እስከ መጋቢት 8 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ49 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።

አርባምንጭ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ 13ኛ እና 14ተኛ ደረጃን ይዘው ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የኢትዮ ኤሌክትሪኳ ዳግማዊት ሰለሞን በ22 ግቦች ትመራለች። ረድኤት አስረሳኸኝ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ13 ጎሎች ትከተላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም