ቀጥታ፡

ትውልዱ የፊቼ ጫምባላላን እሴቶች ሊያስቀጥል ይገባል

ሀዋሳ ፤ መጋቢት 6 /2018 (ኢዜአ)፦ትውልዱ የፊቼ ጫምባላላን እሴቶች በሳይንስና ምርምር በማስደገፍ ሊያስቀጥል እንደሚገባ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር  ደስታ ሌዳሞ ገለጹ። 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለፊቼ ጨምባላላ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

የሲዳማ ዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ በዓል በሀዋሳ "ሶሬሳ ጉዱማሌ" እየተከበረ ነው።


 

የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በበዓሉ ላይ እንደገለጹት፤ የፊቼ ጫምባላላ በዓል የሲዳማ አባቶች የከዋክብትን ኡደት ተከትለው ጊዜን የሚቆጥሩበት የስልጣኔ መገለጫ ነው።

በመሆኑም የፊቼ ጫምባላላን ሀገር በቀል እሴቶች ለትውልድ ለማሸጋገር የአሁኑ ትውልድ በሳይንስና ምርምር የተደገፈ ስራ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

በአሉ  የሰላም፣ የፍቅርና  የይቅርታ እሴቶችን በውስጡ የያዘና የህዝቦችን አንድነትና ትስስር የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።

አብሮነት ለመደመር ሃይል መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ የፊቼ ጫምባላላ በዓል ግጭቶችን በማስወገድ ለይቅርታና ለፍቅር የሚሰጠው ልዩ ቦታ ከልዩነት ይልቅ በአንድነት የመኖርን እሴት የሚያጎላ ነው ብለዋል።


 

በዓሉ ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለተፈጥሮ ጭምር የተለየ ክብር የሚሰጥና ለሀገር ሰላምና አንድነት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጃጎ አገኘሁ በበኩላቸው ፤ በዓሉ በውስጡ የያዛቸውን እሴቶች ለትውልድ ለማስተላለፍ በጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

አባቶች ያቆዩትን ባህል ምሁራን በሳይንሳዊ መንገድ እንዲሰነድ በማድረጋቸው በዓሉ የዓለም ቅርስ መሆኑንና ከአመት አመት በድምቀት እየተከበረ መሆኑን ተናግረዋል።

በዓሉ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የህብረተሰብ ተወካዮች በተገኙበት እየተከበረ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም