ቀጥታ፡

በብሄረሰብ አስተዳደሩ ለመኽር እርሻ የሚውል በቂ የአፈር ማዳበሪያ ቀርቧል

ሰቆጣ ፤ መጋቢት 6 /2018 (ኢዜአ)፦በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ለ2018/19 የምርት ዘመን የሚውል በቂ የአፈር ማዳበሪያ ወቅቱን ጠብቆ መቅረብ መቻሉን የብሄረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በክልሉ የህዝቡን የመልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በተሰራው ስራ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ ነው

የመምሪያው ኃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በመኸርና በመስኖ የሚካሄደውን የሰብል ልማት ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ስራወዎች እየተሰሩ ነው።


 

በዚህም በ2018/19 የምርት ዘመን የሚካሄደውን የሰብል ልማት ምርታማነት ለማሳደግ 40ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ለማስገባት ታቅዶ እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁን በተደረገ ጥረትም ካለፈው ዓመት የተረፈውን ጨምሮ አዲስ የገባ ከ33ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ወደ ብሄረሰብ አስተዳደሩ ደርሶ እየተሰራጨ መሆኑን ተናግረዋል።

የገባው ማዳበሪያ በዋቢ ዩኒየንና በህብረት ስራ ማህበራት በኩል እየተሰራጨ እንደሚገኝ ጠቁመው ቀሪውን ለማስገባት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የአፈር ማዳበሪያ ቀድሞ መድረሱ አርሶ አደሩ በወቅቱ በመዝራትና በመንከባከብ የሚጠበቀውን ምርት ለማምረት የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።

የዋቢ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን የግብይት ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ታረቀ በበኩላቸው፤ የአፈር ማዳበሪያው በዩኒየኑ መጋዘኖች ተከዝኖ ወደ ወረዳዎች እየተጓጓዘ ነው።


 

ወደ ወረዳዎች የሚላከው የአፈር ማዳበሪያም በቀበሌ ህብረት ስራ ማህበራት በኩል ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እየሆነ ነው ብለዋል።

በሰቆጣ ወረዳ 01 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ማሞ አለሙ እንዳሉት የአፈር ማዳበሪያው በወቅቱ መቅረብ መቻሉ ለአርሶ አደሩ ፈጥኖ የእርሻ ስራውን እንዲያከናውን የሚያስችል ነው።

ለግማሽ ሄክታር የእርሻ መሬታቸው የአፈር ማዳበሪያ ቀድመው በመግዛት በወቅቱ ሰብላቸውን እንደሚዘሩም ተናግረዋል።

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በዘንድሮው ዓመት 120ሺህ 638 ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን ተቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም