ቀጥታ፡

በክልሉ የህዝቡን የመልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በተሰራው ስራ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ ነው

ወላይታ ሶዶ፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ):- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህዝቡን የመልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በተሰራው ስራ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ተናገሩ።

በክልሉ የወላይታ ዞን ዳሞት ሶሬ ወረዳ፣ በመንግሥትና በግል ባለሀብቶች ቅንጅት ከ125 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ።

ለአገልግሎት ከበቁት ፕሮጀክቶች መካከል የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የመንገድና የድልድይ እንዲሁም የጤና ተቋማት መሆናቸው ተገልጿል።


 

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የክልሉ መንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላ እንደገለጹት፤ መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር በቅንጅት በመሥራቱ በክልሉ የሕዝቡ የመልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ ነው። 

"ሕዝቡንና የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ከግብ እንዲደርሱና ሁለንተናዊ እድገት እንዲረጋገጥ በትብብር መሥራት ይገባል" ሲሉም አሳስበዋል።

በአጠቃላይ ባለፉት ዓመታት በክልሉ የህዝቡን የመልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በተሰራው ስራ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን አስረድተዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሳሙኤል ተሰማ (ረዳት ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ የሕዝቡን የመሠረተ ልማት ችግሮች ለመፍታት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

በዞኑ በበጀት ዓመቱ ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ከበቁት መካከል የተለያዩ ቀበሌዎችን የሚያገናኝ ከ86 ኪሎ ሜትር በላይ የጠጠር መንገድና 8 ድልድዮች ይገኙበታል ብለዋል። 

በአሁኑ ወቅትም 32 ተጨማሪ ፕሮጀክቶች  በገንባታ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የሕክምና ግብዓት ችግርን ለመቅረፍ ከ384 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መድኃኒቶችና መሣሪያዎች መቅረባቸውን አንስተው ከተገነቡ 21 ሞዴል የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤቶች መካከል 12ቱ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት ጀምረዋል ብለዋል።

በዳሞት ሶሬ ወረዳ የተመረቀው የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት በ6 ቀበሌዎች የሚኖሩ ከ20 ሺህ በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የአካባቢው ነዋሪዎች የሆኑት አቶ አስራት አበበ እና ወይዘሮ ዘማች ሰለሞን፣ ለረጅም ጊዜ የሕዝብ ጥያቄ ሆነው የቆዩ የድልድይና የመድኃኒት ቤት ግንባታዎች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት በመብቃታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል። 

መሰረተ ልማቶቹ ምርታቸውን ወደ ገበያ ለማውጣትና የተሻለ የጤና አገልግሎት ለማግኘት ትልቅ እገዛ እንደሚያደርጉላቸውም ጠቁመዋል።

የሥራ ኃላፊዎቹ ሕብረተሰቡ ለአገልግሎት በቁ የልማት ፕሮጀክቶችን እንደራሱ ንብረት በመቁጠር በባለቤትነት እንዲጠብቃቸው ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም