ከሳምንቱ ዐበይት ክንውኖች መካከል - ኢዜአ አማርኛ
ከሳምንቱ ዐበይት ክንውኖች መካከል
ከየካቲት 23 እስከ 29 ቀን 2018 በሀገር ውስጥ ከተከናወኑ ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ከፊሉ ቀጥለው ተዳሠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ስለ ዓድዋ ድል በዓል
•የዓድዋ ድል ቀን በመላው አፍሪካ እና ጥቁር ሕዝብ ላይ ጨልሞ በነበረ ሰማይ ፀሐይ የፈነጠቀበት መሆኑን 130ኛውን የዓድዋ ድል አከባበር አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ገልጸዋል። ዛሬ የምንኖር ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን እና እናቶቻችን ሞተው ያቆሙልንን ሀገር በአንድነት እና በፍቅር በመኖር ልናስቀጥል ይገባልም ብለዋል። ከእነሱ ተምረን ድህነትን፣ መከፋፍልን እና ኋላ ቀር አስተሳሰብን ዐሻፈረኝ በማለት ኢትዮጵያን ወደ ብልጽና ልናሻግር ይገባልም ነው ያሉት።
•በሌላ በኩል በተጠናቀቀው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በረመዳን መንፈስ፤ ከቡሩንዲ፣ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ከሶማሊያ፣ ከኢራቅ፣ ከሶሪያ፣ ከፍልስጤም፣ ከአፍጋኒስታን፣ ከኤርትራ፣ ከየመን እና ሱዳን ከመጡ ስደተኛ ቤተሰቦች ጋር አፍጥር ታድመዋል።
•እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በትግርኛ ቋንቋ ቆይታ አድርገዋል። በዚሁ ወቅት የትግራይ ሕዝብ ሠላምና ልማት ይገባዋል፣ ሠላምና ልማትም ይወዳል፣ ለሠላምና ለልማት ታግሏል፤ በአንጻሩ ዳግም ጦርነትና ውድመት አይገባውም የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፣ የነበረው ጭቅጭቅ ይታወሳል፤ ነገር ግን ሰላም ነው የሚሻለው ብለን የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ከፍለናል፣ የልዩነቶች መኖር ተፈጥሯዊ ነው ነገር ግን ልዩነቶችን በግጭትና በመሣሪያ ኃይል መፍታት አያዋጣም የሚሉትንና ሌሎች ጉዳዮችን አንስተዋል።
130ኛው የዓድዋ ድል በዓል
•130ኛው የዓድዋ ድል በዓል "ከአኩሪ ታሪክ፤ ወደ ብሩኅ አድማስ" በሚል መሪ ሐሳብ በድምቀት የተከበረው ባሳለፍነው ሣምንት ነበር።
•በዚሁ ወቅትም ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሐውልት እና በዓድዋ ጀግኖች መታሰቢያ የአበባ ጉንጉን ካኖሩ በኋላ ንግግር አድርገዋል። በንግግራቸውም፤ የዓድዋ ብሩኅ መንፈስ የሚጸየፈውን ቅጥረኝነት በማስወገድና ብሔራዊ ጥቅምን በማስቀደም ኢትዮጵያን በዓለም ዐደባባይ ከፍ እናድርግ ብለዋል።
•ኢትዮጵያ የምታሸንፈው በልጆቿ ብርታትና በሐሳቧ ልዕልና መሆኑን አስገንዝበው፤ የሐሳብና የዕውቀት ትግሉ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል። በጥቁር ሕዝቦች ዘንድ "ሰው በሰውነቱ ነፃ ነው" በሚል በተቀመጠው የኢትዮጵያ የመገለጥ ድርሳን እና ኢትዮጵያን ዓለም ባደነቃት ልክ ከፍ ልናደርጋት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ
•53ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ የተካሄደው ባሳለፍነው ሳምንት ሲሆን፤ በተለያዩ ዐበይት ጉዳዮች ላይ ተወያቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል። በዚህም መሠረት፤ በመደመር የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ፣ ለባለሃብቶች ካሳ ለመክፈል ግዴታ የሚገባበትን ሁኔታ ለመወሰን በቀረበ ደንብ፣ በሦስት የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነቶች፣ የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት ረቂቅ ደንብ፣ የወርቅ ማዕድን እና የብረት ማዕድን ምርት ፈቃድ ረቂቅ ስምምነቶች እንዲሁም የቱሪዝም ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
48ኛው የካራማራ ድል
•ባሳለፍነው ሳምንት ከተከናወኑ ዐበይት ጉዳዮች አንዱ "በካራማራ ያገኘነው ድል በቀይ ባሕር ይደገማል" በሚል መሪ ሐሳብ የተከበረው 48ኛው የካራማራ ድል በዓል ነው።
•የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ሌተናል ጀነራል አዲስ ተድላ በአከባበሩ ላይ፤ የካራማራ ድል ኢትዮጵያውያን በውስጥ ችግሮች ቢኖሩ እንኳ፤ በሀገር ላይ ለሚመጣ ማንኛውም ዓይነት ጥቃት በጋራ እንደሚመክቱ ለዓለም ያስመሰከሩበት ነው ብለዋል። የአባቶቹ ልጅ የሆነው የአሁኑ ትውልድም በልማትና በሀገር ጥቅም ማስከበር ረገድ ዝግጁ በመሆኑ ኩራት እንደሚሰማቸው አንስተዋል።
የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ጉብኝት
•ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ አካባቢ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ሠራዊት ሙዝየም ባሳለፍነው ሳምንት ጎብኝተዋል። በጉብኝታቸውም በሙዝየሙ የዘመናት የጀግንነት ጉዞን የሚመሠክሩ ኅያው ዐሻራዎችን መመልከታቸውን በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው አስፍረዋል።
•የኢትዮጵያ ሠራዊት ሙዝየም የጀግንነታችን ማኅደር የልዕልናችን ምሥክር ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሙዝየሙ ከትናንቱ እንማርበታለን፤ ዛሬን እንገመግምበታለን፤ ለነገ ደግሞ እናቅድበታለን ብለዋል።
•አፍሪካውያንና መላው በፀረ ቅኝ አገዛዝ የታገለ የዓለም ሕዝብ ሁሉ ይህን ሙዝየም በመመልከት የራሱን ታሪክ እንዲያደንቅም ጋብዘዋል።
የመራጮች ምዝገባ መጀመር
•በግንቦት ወር ለሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ተጀምሯል። ምዝገባው ለአንድ ወር የሚቀጥል ሲሆን፤ በመደበኛ የመራጮች ምዝገባ፣ ምርጫዬ በተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ እና በድረ ገጽ እንዲሁም በአካል በመገኘት በሚደረግ የዲጂታል ምዝገባ እየተከናወነ ነው።
•የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በሰጡት መግለጫ፤ 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች 10 ሺህ 934 ዕጩዎች ማስመዝገባቸውን አስታውቀዋል። ከዚህ ውስጥ 2 ሺህ 198 ዕጩዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም 8 ሺህ 736 ለክልል ምክር ቤቶች መመዝገባቸውንም ጠቅሰዋል። በሌላ በኩል በግል በዕጩነት ከቀረቡት 73 ሰዎች መካከል 69 ወንድ ቀሪዎቹ ሴቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።