የሃይማኖት ተቋማት በክልሉ ሰላም፣ ልማትና አብሮነት ላይ የሚያከናውኑትን አስተዋጽኦ ማጠናከር አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖት ተቋማት በክልሉ ሰላም፣ ልማትና አብሮነት ላይ የሚያከናውኑትን አስተዋጽኦ ማጠናከር አለባቸው
ሐረር፤ መጋቢት 4/2018(ኢዜአ)፦የሃይማኖት ተቋማት በክልሉ ሰላም፣ ልማትና አብሮነት ላይ በትብብር የሚያከናውኑትን አስተዋጽኦ ማጠናከር አለባቸው ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።
የኃይማኖት ተቋማት ለሰላምና አብሮነት የሚተጋ ትውልድን በማፍራት ረገድ እያደረጉት ያለውን አስተዋፅኦ ሊያጠናክሩ ይገባል
“የመደመር መንግሥት እና የሃይማኖት ተቋማት” በሚል መሪ ሀሳብ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የሃይማኖት አባቶች የተዘጋጀ ክልል አቀፍ የምክክር መድረክ በሐረር ተካሂዷል።
በምክክር መድረኩ ላይ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እንዳሉት፤ ሀገር የሚገነባው በሁሉም አስተዋጽኦ እና ተሳትፎ ነው።
በክልሉ የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማትም በሁሉም ዘርፎች ከመንግስት ጋር ተቀራርበው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ሰላምን በማረጋገጥና በክልሉ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎችን በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን ሚና እየተወጡ እንደሚገኙም አንስተዋል።
በዚህም በሰላም ግንባታ፣ በልማት፣ በብልጽግና ጉዞና እድገት ላይም አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ጠቁመው በሚያከናውኑት ስራ ውጤት መታየቱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያንም ትውልድን በመገንባት፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና እድገት፣ በህዝብ ለህዝብ ትስስርና በሌሎች አበረታች ተግባራት ማከናወኗን ተናግረዋል።
መንግሥትም ለሃይማኖት ተቋማት መጠናከርና መጎልበት በርካታ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስታውሰዋል።
በክልሉ በሁሉም መስክ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ማጠናከር ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የሃይማኖት ተቋማትም በክልሉ ሰላም፣ ልማትና እድገት ላይ የሚያከናውኑትን አስተዋጽኦ ማጎልበት ይገባል ብለዋል።
በእምነት ተቋማት መካከል ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን በማጎልበት በመቀራረብና በአብሮነት መስራትን አጠናክረው ማስቀጠል እንደሚገባም አመልክተዋል።
በውይይቱ ተሳታፊ የሆኑት የሃይማኖት አባቶችም ፤ የክልሉ መንግስት ከሃይማኖት ተቋማት ጋር ተቀራርቦ እየሰራ ላለው ተግባር ምስጋና አቅርበዋል።
ከዚህ ባለፈም በክልሉ የሚከናወነው የኮሪደርና ሌሎች የልማት ስራዎች ከተማዋን እያስዋበና ለነዋሪው እርካታ እያጎናፀፈ በመሆኑ ተግባሩን አወድሰዋል።
በቀጣይም ከመንግስት ጎን በመሆን የተጀመሩትን የልማት፣ የሰላምና የአብሮነት ስራ ትኩረት ሰጥተው እንደሚደግፉም አረጋግጠዋል።
በመርሐ-ግብሩ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የቤተ እምነቱ መሪዎች፣ ካህናትና ሌሎችም ተሳትፈዋል።