ቀጥታ፡

የኃይማኖት ተቋማት ለሰላምና አብሮነት የሚተጋ ትውልድን በማፍራት ረገድ እያደረጉት ያለውን አስተዋፅኦ ሊያጠናክሩ ይገባል

ሀዋሳ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ የኃይማኖት ተቋማት ለሰላምና አብሮነት የሚተጋ ትውልድን በማፍራት ረገድ እያደረጉት ያለውን አስተዋፅኦ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ተናገሩ።

የሃይማኖት ተቋማት የሰላም ግንባታና የልማት ስራዎች ላይ ያላቸውን አስተዋፅኦ ሊያጠናክሩ ይገባል

ርዕሰ መስተዳድሩ "የመደመር መንግስት በሀይማኖት ተቋማት ዕይታ" በሚል መሪ ሀሳብ በክልሉ ከሚገኙ የሀይማኖት ተቋማት ከተወጣጡ የሀይማኖት አባቶች ጋር ተወያይተዋል።


 

በውይይቱ ወቅትም ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት፤ የኃይማኖት ተቋማት ለሰላምና አብሮነት የሚተጋ ትውልድን በማፍራት ረገድ እያደረጉት ያለውን አስተዋፅኦ ሊያጠናክሩ ይገባል።

በተለይም የህዝቦችን ትስስር የሚያጠናክሩ የአንድነትና አብሮነት ዕሴቶችን በማስረጽ ትውልዱን በመልካም ሥነ-ምግባር የማነጽና የመቅረጽ  ሃላፊነታቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት የሀይማኖት ተቋማትን ጨምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ሰላምን ማረጋገጥና የልማት ትሩፋቶች ማየት መቻሉን አንስተው ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

በዚህም ተቋማቱ ትውልዱ ሀገር በቀል ዕሴቶችን የሚያከብርና በመልካም ስብዕና ተገንብቶ እንዲያድግ እያደረጉ ያለውን አስተዋፅኦ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡ 

የሀይማኖት ተቋማት በክልሉ ላለው ሰላምና አብሮነት ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሲዳማ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ዳንጊሳ ናቸው። 


 

ይህም ለክልላዊ ልማትና ዕድገት መፋጠን ዓይነተኛ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰው ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሀይማኖት ተቋማትና አባቶች የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ማጠናከር እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ ቄስ ኢያሱ ጠጊቾ በበኩላቸው፤ የክልሉ መንግስት የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱን አድንቀው ለሰላምና ለህዝቦች አንድነት መጠናከር የምናደርገውን ጥረት እናጠናክራለን ብለዋል።


 

መንግስት የሀይማኖት ተቋማት ተቀራርበው በመስራት ለሰላምና ልማት መጠናከር እየተወጡ ያለውን ኃላፊነት እንዲያጠናክሩ እያደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ ለተግባራዊነቱ እንተጋለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የማዕከላዊ ሲዳማ ዞን የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ፓስተር ታደሰ ሀሰን፤ ተቀራርበን በመስራት ክልሉን ሰላም ማድረግ ችለናል ብለዋል።

ይህንንም አጠናክረን በማስቀጠል ህዝቡን በማስተማርና በማስገንዘብ ረገድ ተቀናጅተን እንሰራለን ሲሉም አረጋግጠዋል።

በውይይት መድረኩም ከተለያዩ የሀይማኖት ተቋማት የተውጣጡ አባቶችና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም