ቀጥታ፡

በክልሉ የዲጂታል 2025 ምርጥ ተሞክሮን በማስፋት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ተግባራዊ እየተደረገ ነው

ባህር ዳር ፤ መጋቢት 4/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል የዲጂታል 2025 ምርጥ ተሞክሮን በማስፋት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 በተሻለ መልኩ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ገለፀ።

የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ እውን እንዲሆን የዜጎችን ክህሎትና እውቀት ማሳደግ ላይ በትኩረት መስራት ይገባል

ምክትል ቢሮ ኃላፊው የቻለ ይግዛው እንዳሉት፤ በክልሉ በ2025 ዲጂታል ኢትዮጵያ የተገኘውን ምርጥ ተሞክሮ በማስፋት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ተግባራዊ መደረጉም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አሰራራቸውን በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ የህዝብ ቅሬታን መፍታት እንዳስቻላቸው ነው ያረጋገጡት።

ተሞክሮው በቀጣይ አምስት ዓመታት ለሚደረግ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መሳለጥና ማደግ የጎላ አበርክቶ እንደሚኖረው ገልፀዋል።

በተጨማሪም ከአድሎ የፀዳ አሰራርን እውን በማድረግ የተጠቃሚውን እርካታ ከፍ የሚያደርግ መሆኑንም አስረድተዋል።

በክልሉ በርካታ ተቋማት አሰራራቸውን ዲጂታላይዝ ማድረግ መቻላቸውን ጠቅሰው፤ ይህ የዲጂታላይዜሽን ትራንስፎርሜሽን ትግበራ የተሻለ ውጤት ታይቶበታል ብለዋል።

በተለይም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ትግበራ ሰፊ የህዝብ ቅሬታዎችን በአጭር ጊዜ ለመፍታት ያስቻለ እንደሆነ ገልፀዋል።

እንዲሁም የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ በቴክኖሎጂ ታግዞ እየተከናወነ ያለና የተለያዩ አገልግሎቶችን እያዘመነ መሆኑን አብራርተዋል።

ዘመኑ ቴክኖሎጂን አብዝቶ መጠቀምን የሚጠይቅና ለዚሁ የሚሆን ምህዳር መፍጠር የግድ በመሆኑ በዘርፉ በተከናወኑ ተግባራት እመርታዊ ለውጥ እየታየ ነው ብለዋል።

በቀጣይም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ትግበራን በሁለንተናዊ መንገድ ጥቅም ላይ ለማዋልና እንደ ሃገር የሚጠበቀውን ውጤት ለማስመዝገብ በጋራ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም